ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – ኢራን በዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ አምስት ዜጎቿን በተቀናጀና ከፍተኛ ዝጅግት በተደረገበት ሁኔታ አፍና ጠልፋ ለመውሰድ የሸረበችው ሴራ መክሸፉን የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢራን ልትጠልፋቸውና አፍና ወደ አገሯ ወይም ወደ ወዳጅ አገር ቬንዝዌላ ልታሻግራቸው የነበሩት አምስት ዜጎቿ የኢራንን ኢስላማዊ አስተዳደር በመተቸት ከፍ ያለ እውቅናና ተሰሚነት የነበራቸው እንደሆኑ ተገልጿል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የታፋኞቹን ማንነት ለጊዜው ይፋ ባያደርግም ዕውቋ ደራሲ ማሲህ አሊነጃድ ግን ‘አንደኛይቱ ታፋኝ እኔ ነበርኩ’ ብላለች።
ደራሲ ማሲህ አሊነጃድ መኖሪያዋ በኒው ዮርክ ብሮክሊን ሲሆን፣ የኢራን ኢስላማዊ መንግሥትን በሰላ ብዕሯ በመኄስ ትታወቃለች።
ከእርሷ ጋር ሌሎች በዩኬና በካናዳ የሚኖሩ ሰዎችም በተመሳሳይ ሊታፈኑ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ ነበር ተብሏል።
ለፍትሕ ሚኒስቴር የቀረበው የማንሐታን ክስ እንዳመላከተው አራቱም ከአፈና ሴራ የተረፉት ኢራናዊያን በኢራን መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቁ ናቸው።
አፈናው የታቀደው እነዚህ ሰዎች ወደ ሦስተኛ አገር እንዲሄዱ በማባበል ካግባቡ በኋላ በድጋሚ አፍኖ ወደ ኢራን መመለስ ነበር። ይህን ለማሳካትም ኢራን ለሚኖሩ ታፋኝ ቤተሰቦቻቸው ጭምር የገንዘብ ጉርሻ ተሰጥቷቸው ነበር ተብሏል።
ይህንን አፈና ለማሳካት የተመደቡ ሰዎች የግል መርማሪዎችን ጭምር ቀጥረው የነበረ ሲሆን፣ የግል መርማሪ ቡድኑ ሥራም በኒው ዮርክ ብሮክሊን ነዋሪ የሆነችውን ኢራናዊት ደራሲ በቅርብ ሆኖ መሰለል ነበር። ለዚህ እንዲረዳ በታፋኞቹ የመኖርያ ቤታቸው በከፍተኛ ጥራት ቪዲዮ የሚቀርጽ ረቂቅ መሣሪያዎች በድብቅ ተገጥመው ነበር።
ታፋኞቹን ወደ ቬንዝዌላ የሚወስዱ መጓጓዣ ትራንስፖርቶችም ምቹ ሆነው ሳለ ነው ኤፍቢአይ ሴራውን የደረሰበት ተብሏል።
የኤፍቢአይ የኒው ዮርክ ቢሮ ኃላፊ “ይህ ነገር የተጋነነ የፊልም ታሪክ ያለው ይመስላል” ሲሉ የአፈናውን ድራማ ውስብስብነት ገልጸዋል።
ጸሃፊዋ ማሲህ አሊነጃድ በኢራን መንግሥት እሷን ለማፈን የተደረገው ይህ ሁሉ ዝግጅት የሚያሳየው ‘የኢራን መንግሥት ምን ያህል እኔን እንደሚፈራኝ ነው’ ብላለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።