በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 7 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ-ግብር እየተካሄደ ነው

አቶ አሻድሊ ሃሰን

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዛሬው ዕለት ብቻ 7 ሚሊዮን ችግኞች በመተከል ላይ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ፡፡

ርዕሰ-መስተዳድሩ ከመከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም እና ሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን በአሶሳ ወረዳ ጋምቤላ ቀበሌ ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል፡፡

አቶ አሻድሊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በክልሉ መላው አካባቢዎች በዛሬው ዕለት ብቻ 7 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሃ-ግብር እየተከናወነ ነው፡፡

ክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተፋሰስ አካባቢ በመሆኑ፣ እየተተከሉ ያሉ ችግኞች ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

“ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ-ሃሳብ ለሚከናወነው 3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እንደክልል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ለደን ሽፋን የሚያግዙና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በችግኝ ተከላው ላይ የታየው የህዝብ  ተሳትፎ በእንክብካቤው ላይ እንዲደገምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም በበኩላቸው  በህዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አረንጓዴ አሻራቸውን  ማሳረፋው ልዩ ትርጉም እንዳለው  ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ የሀገርን ሠላም ከማስጠበቅ ባለፈ የልማት ሠራዊት ነው ያሉት ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም፣ በመላ ሀገሪቱ እየተከናወነ ባለው የችግኝ ተካለ መርሃ-ግብር ላይ አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ 72 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስት  ኮሙዩኒኬሽን  ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው  መረጃ  ያመለክታል፡፡