ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ የሚመራ ልዑክ ከኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በሁለትዮሽና በቀጣናው ሠላም ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ትላንት ማምሻውን ወደ ኬንያ አቅንቷል።
የተቋሙ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት፣ ልዑኩ በናይሮቢ በሚኖረው የአራት ቀናት ቆይታ ከኬንያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በሁለትዮሽና በቀጣናው ሠላም ዙሪያ ውይይቶች እና የልምድ ልውውጦች ያደርጋል።
በተለይም ልዑኩ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የኬንያ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም ላሳየው አቋም ምስጋና እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት እና የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግና በኬንያ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሀገር ውጭ ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛውን ቅርንጫፍ ለማቋቋም እንደሚመክር ጠቅላይ ጸሐፊው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡