ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራዝ በሚያስተዳድራቸው መንገዶች በ2013 በጀት ዓመት 327 የትራፊክ አደጋ መድረሱ አስታወቀ፡፡
በትራፊክ አደጋው 15 ሰዎች ለሞት 78 ለከባድ አደጋ የተዳረጉ ሲሆን በሚሊየን የሚቆጠር ንብረት መውደሙ ታውቋል፡፡
በፍጥነት መንገዶቹ ለተገልጋዮች የሚሰጠውን ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት የትራፊክ አደጋ፤ የፍጥነት መንገዶቹ አጥሮች መሰረቅና እንስሰት ወደ መንገዱ መግባት ተግዳሮት ሆነውብኛል ያለው ተቋሙ ከድሬ ደዋ ደወሌ ባለው የፍጥነት መንገድ ከተፈቀደው ክብደት በላይ የሚጭኑ ተሸከርካሪዎች መንገዱ ላይ ችግር እያደረሱ መሆኑንም በተለይ ለዋልታ ገልጿል፡፡
ከፍጥነት በላይ ማሽከርከርና የቴክኒክ ችግር ባለባቸው ተሽከርካሪዎች የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ በመንገዶቹ ላይ በደረስው ጉዳት ለመንገድ ጥገና ብቻ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ስለመደረጉም ተገለጿል፡፡
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በመንገዶች ያለውን የትራፊክ ፍሰት በደኅንነት ካሜራ ቁጥጥር ስር አድርጓል፡፡
በመንገዶች ላይ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ለመስጠት ከዚህ በፊት ከነበረው አንቡላስ አገልግሎት በተጫማሪ በ8 ሚሊዮን ብር ሶስት ዘመናዊ አንቡላሶችን መገዛታቸውም ተገልጿል፡፡
ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ወደ ፈጣን መንገዶች የሚገቡ አሽከርካሪዎች የትራፊክ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
(በምንይሉህ ደስይበለው)