ሀገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናትና የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄድ ነው

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – 3ኛው ሀገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናትና የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄድ ነው፡፡

በአውደ ጥናቱ ሙስና በሀገሪቱ የመንሰራፋቱ ምክንያት ምንድን ነው? የትኞቹ ተቋማት ናቸው  ይበልጥ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑት እንዲሁም ከሙስና የፀዳ ሀገር እንዴት መፈጠር ይችላል  የሚሉና መሰል ጥናቶች እየቀረቡ ነው።

የሙስና ወንጀሎች ለመከላከል የግልፀኝነትና ተጠያቂነት አሰራርን መተግበር እንደሚገባ ተነግሯል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት ምክትል አፈ ጉባኤዋ ሽታዬ ምናለ በመዋቅር ተደግፈው  የሙስና ወንጀሎች ሲፈፀምባቸው የነበሩ ተቋማት፣ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በዜጎች ተሳትፎ የሚገነቡ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሙስና ወንጀሎች መፈፀማቸውን ገልፀው፣ በዛሬው ዕለት የሚካሄደው አውደ ጥናት የሀገሪቱ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ወደ ፊት ያራምዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል ሙስናን ለማጥፋት የተለያዩ ጥረቶች ቢታዩም አሁንም 87 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በአቋራጭ ለመክበር ምኞት እንዳላቸው ተጠቁሟል።

በጥናቶቹ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይበልጥ ለሙስና ተጋላጭ እንደሆኑም ተገልጿል።

(በዙፋን አምባቸው)