ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለ1 ሺህ 442ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ1 ሺህ 442ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለ1442ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል የመታዘዝና የመስዕዋት በዓል ነው። ነቢዩ ኢብራሒም ለፈጣሪያቸው ያላቸውን መታዘዝ ያሳዩበት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) “ልጅህን ሰዋልኝ” ብሎ ሲያዝዛቸው አንድያ ልጃቸውን እስማኤልን ለመሰዋት ቅንጣት ታህል አላመነቱም። ይኼን ማድረግ ቀላል አይደለም፤ ድፍረትና ጽናትን ይጠየቃልና በሙስሊሙ ዘንድ የነብዩ ኢብራሒም ታሪክ ልዩ ትርጉም አለው።
መታዘዝ የበታችነት ስሜት አይደለም። ራስን በሥነ ሥርዓት የመግዛት ውጤት እንጂ። ዋናው ጉዳይ ለማን መታዘዝ እንዳለብን ማወቅ ነው። በየመሥሪያ ቤቶቻችን ውስጥ ለትክክለኛው መመሪያ፣ አሠራርና አቅጣጫ ታዝዞ ያለመሥራት አንዱ ፈተናችን ነው። ነቢዩ ኢብራሂም የታዘዙትን ለመፈጸም ያጋጠማቸውን ፈተና ሁሉ አልፈውታል።
ምክንያትም ሆነ ሰበብም ላለመስጠት ከራሳቸው ጋር ታግለዋል። ዓላማቸው የታዘዙትን መፈጸም እንጂ ለምን እንደማይቻል ምክንያት መፈለግ አልነበረም። በሀገር ጉዳይ ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ ይሄንን ዕሴት ልንላበሰው ይገባል።
የዘንድሮውን የዐረፋ በዓል የምናከብረው እንደ ሀገር በሁለት አቅጣጫዎች እየተፈተንን ነው። እስከ አሁንም እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገናል፤ መስዕዋትነት ከፍለናል። በአንድ በኩል በሕዳሴ ግድባችን ዙሪያ የዘመናት ምኞታችን እውን እንዲሆን፣ የዓመታት ልፋታችን ፍሬ እንዲያፈራ የመጨረሻውን ተጋድሎ በማድረግ ላይ እንገኛለን።
በሌላ በኩል አንድነታችንን ከሚሸረሽሩና ሀገራችንን ከጀርባ እየወጓት ከሚገኙ እኩይ ኃይሎች ጋር እየተፋለምን ነው። አሁን ለሀገራችን ያለንን ጥልቅ ፍቅር በተግባር የምናሳይበት ወሳኝ ወቅት ነው። በሀገር ጉዳይ እስከ ምን ድረስ ለመፈተን ዝግጁዎች መሆናችንን ልናስመሰክር ይገባል።
የመጨረሻዋ የመስዋት ሰዓት በደረሰች ጊዜ ነብዩ ኢብራሒምና ልጃቸው እስማኤል የተሰማቸው ጭንቀት እጅግ ከባድ ነበር። ነገር ግን ፈተናው አላሸነፋቸውም፤ በድል ተወጥተውታል። እኛም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አስጨናቂውን ጊዜ በድል እንደምንወጣው አልጠራጠርም።
የሚገጥሙንን የዲፕሎማሲና ሁለንተናዊ ጫናዎች ተቋቁመን በጽናት እንጓዛለን። እስከ አሁን አንደኛውና ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በድል ማጠናቀቅ ችለናል። በዚህ መልኩ እውነትን ይዘን በትብብርና በመናበብ መጓዛችንን ከቀጠልን ያለጥርጥር ፍጻሜአችን ያምራል።
በዚህ አጋጣሚ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆናችሁ በሕዳሴ ዙሪያ ስትፋለሙ ለነበራችሁ ሁሉ ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ። ሀገር ፍቅራችሁን በምትሻበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ከጎኗ በመቆማችሁ፣ አስፈሪ የሚመስሉ ተገዳዳሪዎቿን በድፍረት በመጋፈጣችሁ፣ በኢትዮጵያ ስም ሳላመሰግናችሁ አላልፍም። ወደፊትም አይተኬ ሚናችሁን አጠንክራችሁ እንደምትገፉበት ተስፋ አለኝ።
የዛሬውን የመስዕዋት በዓል ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን በምናከብርበት በዚህ እለት፣ ሀገራችንን አደጋ ላይ እየጣላት የሚገኘውን የጁንታ ሐይል ለመፋለም በዱር በገደሉ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙ ወገኖቻችን አሉ። ዐረፋን ስናከብር እነዚያን መስዕዋት የሚሆኑ ወንድሞቻችንን እያሰብንና ተገቢውን ክብር እየሰጠናቸው መሆን አለበት። ዛሬ እነሱ የሚቀበሉት መከራ ትላንት በጁንታው ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ለዓመታት ተራርቀው የሚገኙ ወንድሞቻችንን ይመልሳል፤ ፍቅርና መተሳሰብን ያመጣል፤ ከምንም በላይ እንደ ሐገር በአንድነት ጠንክረን እንድንቆም ያደርጋል።
የተከበራችሁ ሙስሊም ወንድም እህቶቼ፣
የዐረፋ በዓል የመስዕዋት ብቻ ሳይሆን የመተጋገዝና የመደጋገፍ በዓል ጭምር ነው። ሕዝበ ሙስሊሙ ደስታና ሐዘኑን እየተጋራ በዓሉን በአንድነት ያከብራል። የዐረፋ ሰሞን አንድም ሰው ተርቦና ተጠምቶ፣ ታርዞና ተከፍቶ አያሳልፍም። በዐረፋ ከሚከናወነው እርድ አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች እንዲሰጥ የእስልምና አስተምህሮ ያዛል።
በዓሉ በዓል የሚሆነው ሙኢምኑ ተረዳድቶና አንድ ሆኖ ሲያከብረው ነው። መረዳዳትና መተሳሰብ ሀገርን ከፈተና የሚያወጣና ወደምትፈልገው ደረጃ የሚያደርስ ዕሴት ነው።
ኢትዮጵያውያን ያለንን ሁሉ አውጥተን፣ የተማሩ ላልተማሩ፣ ያላቸው ለሌላቸው፣ የሚችሉ ለማይችሉ፣ የተረዱ ላልተረዱ አካፍለው ይሄን ያለንበትን ፈታኝ ጊዜ ማለፍ እንዳለብን አረፋ ያስተምረናል።
የዐረፋ በዓል አዳምና ሔዋን የተገናኙበት የአንድነት በዓልም ነው። አንድነት የሰው ልጅ ዘመናትን ተሻግሮ፣ የገጠሙትንም ፈተናዎች አልፎ ዛሬ ለደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ ያበቃው ዕሴት ነው።
የሰው ልጅ የትራንስፖርትና የመገናኛ መሣሪያዎችን ሲፈለስፍ የኖረው፣ ዓለምን ለማሰስ ዋጋ የከፈለው፣ ከሌላው ጋር አንድ ካልሆነ በቀር ህልውናው ከአደጋ እንደማይጸዳ ስለተረዳ ነው።
የዐረፋን በዓል ስናከብር እኛ ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን አጥብቀን መቆም እንዳለብን እናስባለን። አንድነቱን ያጸና ሕዝብ በማንኛውም ፈተና ፊት ብርቱ ሆኖ ይቆማል። ማንኛውንም ተግዳሮት አሸንፎ ያልፋል። ማንኛውንም መሻቱን በጥረቱ ይደርስበታል።
ጠላቶቻችን አንድ ሆነው እየመጡ ነው። ኢትዮጵያን የማፍረስ አንድ ግብ ይዘው እየመጡ ነው። ዐቅማችንን፣ ዕውቀታችንን፣ ዕሴቶቻችንንና ጉልበታችንን ካስተባበርን፣ አንድ ሆኖ የመጣን ጠላት አንድ ሆነን ድል ማድረግ እንችላለን።
መጭው ጊዜ ለሀገራችን የደስታና የበረከት እንዲሆን ከዐረፋ በዓል ያገኘናቸውን ዕሴቶች በሁሉም ዘርፎች እንደምንተገብራቸው እተማመናለሁ። እንዲያ ስናደርግ የሚፈትኑን መከራዎች ሁሉ የሚታለፉ፣ ጠላቶቻችን ሁሉ በቀላሉ የሚሸነፉ፣ የምንመኘው ብልጽግና በፍጥነት የሚሳካ ይሆናል።
በድጋሚ መልካም የዐረፋ በዓል እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ፣ በእለቱ ድኾችን፣ በየመጠለያው ያሉ ወገኖችን፣ በየሕክምና ማዕከሉ ያሉትን ሕሙማን እንድናስባቸው አደራ እላለሁ፡፡
ዒድ ሙባረክ!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሀምሌ 12፣ 2013 ዓ.ም