በቻይና ባጋጠመ ከባድ ጎርፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወጡ

በቻይና ያጋጠመ ከባድ ጎርፍ

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – በማዕከላዊ ቻይና የጣለ ከባድ ዝናብ ጎርፍ በማስከተሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወጡ። የባቡር ጣቢያዎችና መንገዶችም በጎርፉ ተውጠዋል።

በሔናን ግዛት ከፍተኛ ነው በተባለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው ጊዜያዊ መጠለያ ለመግባት ተገደዋል።

የጎርፍ አደጋው ከተከሰተ ጀምሮም ዠንግዡ ከተማ ውስጥ ብቻ ቢያንስ 12 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

በርካታ ከተሞች በጎርፉ የተጥለቀለቁ ሲሆን፣ መንገዶች ተዘግተዋል፤ በረራዎችም ተሰርዘዋል።

የ94 ሚሊየን ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ሔናን ግዛት ያልተለመደውን የዝናብ ወቅት ተከትሎ ከባድ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

ለጎርፍ አደጋው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የተነገረ ሲሆን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተ ሞቃታማ ከባቢ አየር ከባድ ዝናብ እንዲፈጠር ሳያደርግ አይቀርም ተብሏል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ ምሥሎች መንገዶች በጎርፍ ተጥለቅልቀውና በፍጥነት የሚጓዘው ጎርፍ ላይ መኪኖችና ሌሎች ፍርስራሾች ሲንሳፈፉ ያሳያሉ።

በሔናን ግዛት ያለውና በቅርቡ በተከሰተው ከባድ ዝናብ ጉዳት ያጋጠመው ግድብም ሊደረመስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተገልጿል።

በሉያንግ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ይህ ግድብ 20 ሜትር የሚሆነው ግንብ ተገምሶ መታየቱን ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ወታደሮችም ወደ አካባቢው የተሰማሩ ሲሆን፣ ግድቡ በማንኛውም ሰዓት ሊፈርስ እንደሚችል ጦሩ አስጠንቅቋል።

በዠንግዡዋ ደግሞ ያልተረጋገጠ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል በጎርፍ በተጥለቀለቀ ባቡር ውስጥ መንገደኞች ትከሻቸው ድረስ በጎርፉ ተውጠው ያሳያል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችም በገመድ በመሳብ ሰዎችን ሲጎትቱ፤ አንዳንዶቹም በጎርፉ ከመዋጥ ለመዳን በባቡሩ መቀመጫዎች ላይ ቆመው ታይተዋል።

እስካሁን በጎርፍ አደጋው ሳቢያ መውጣት አቅቷቸው ባሉበት የቀሩ ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ አይታወቅም። ይሁን እንጂ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአደጋው ማትረፍ እንደተቻለ ተነግሯል።

በዠንግዡ ባለፉት ሦስት ቀናት የጣለው የዝናብ መጠን ዓመቱን በሙሉ ከሚጥለው የዝናብ መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ከባድ ዝናብም ቢያንስ ለ24 ሰዓታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መተንበዩን ቢቢሲ ዘግቧል።