በሶማሌ ክልል ለህወሀት ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ 28 ግለሰቦችና ንብረቶቻቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ


ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – ለህወሀት ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ 28 ግለሰቦችና ንብረቶቻቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ::
በሶማሌ ክልል የሚገኙ የጁንታው ተላላኪዎች ለቡድኑ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለፁት የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ረ/ኮሚሽነር መሀመድ አሊ ሐሰን 28 ግለሰቦች፣ 10 የሲኖትራክ መኪና እና ሌሎች ንብረቶቻቸው በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ በተደረገ ከፍተኛ ክትትል መያዛቸውን ገልፀዋል።
ግለሰቦቹ በክልሉ ብጥብጥ ለማስነሳት አቅደው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም ነው ረዳት ኮሚሽነሩ የገለፁት።
ለዚህ ተግባር እንዲያብሩ ከዚህ ቀደም የነበረው አመራር አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ የክልሉ ተወላጆችን በማስተባበር ሲሰሩ ቆይተዋልም ብለዋል ረዳት ኮሚሽነሩ።
በተለይ የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ፖሊስ ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ወደ ግዳጅ ማምራቱን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ የጁንታው ተላላኪዊች ይህንን ሀገራዊ ሀላፊነት ሌላ ቅጥያ ስም በመስጠትና በማህበራዊ ሚዲያ ለፕሮፖጋንዳነት በመጠቀም ሂደቱን ለማስተጓጎል ሲጥሩ ነበርም ብለዋል።
የክልሉ ልዩ ሀይል ፖሊስ የሀገሪቷን ሉዓላዊነት እና ህገ መንግስት ለመጠበቅ የገባውን ቃለ መሀላ ለመተግበር ዛሬም ሆነ ነገ ዝግጁ ነው ያሉት ረ/ኮሚሽነሩ ጁንታው ስርዓተ ቀብሩ እስኪፈፀም ድረስም ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመሆኑም በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ እጃቸውን በማስገባት ለጁንታው ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ግለሰቦችና በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና ንብረቶቻቸውን በመሸሸግ እየተባበሩ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሲሉ ረ/ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ሲል ኢብኮ ዘግቧል።
ከዚህ በኋላ በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ የተገኘ ግለሰ ወይም ብድን ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ነው ረ/ኪሚሽነሩ በንግግራቸው ያስታወቁት።