አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳውን ወደ ሌሎች ክልሎች በማስፋቱ የእርዳታ እህል ለማጓጓዝ አስቸጋሪ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳውን ወደ ሌሎች ክልሎች በማስፋቱ የእርዳታ እህል ለማጓጓዝ መቸገሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ሲል ያሳለፈውን የተናጠል ተኩሱ አቁም አሸባሪው ህወሓት ወደ ጎን በመተው ትንኮሳውን ወደ አማራ እና አፋር ክልል በማስፋቱ የእርዳታ እህልና መሰል ድጋፎችን ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት መቸገሩን ድርጅቱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሀቅ እንደገለጹት፤ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት በተሽከርካሪዎች ሲጓጓዝ የነበረውን የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ ክልል ማስገባት አልተቻለም።

ቃል አቀባዩ አያይዘው እንደተናገሩት፤ የእርዳታ ሰራተኞችን፣ ምግብ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ሰብአዊ አቅርቦቶችን የጫኑ ከባድ መኪናዎች ከሰመራ ከተማ ወደ ትግራይ በሚወስደው መንገድ ላይ ተዘግቶባቸው መንቀሳቀስ አልቻሉም።

ቃል አቀባዩ እንደገለጹትም በዚሁ ችግር ምክንያት እርዳታ ለሚፈልጉ የትግራይ ክልል ተረጂዎች መድረስ አልተቻለም።

በቀጣይ ቀናት የረድኤት ሰጪ ሰራተኞችን እና እንደ ነዳጅ ያሉ አቅርቦቶችን ወደ ትግራይ ማስገባት ካልተቻለ አንድ አንድ ሰብአዊ ድጋፎች እንደሚቋረጡም ያለውን ስጋት ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

ድጋፉን በአውሮፕላን ለማድረግ በመንግስት በኩል እድሉ እንደተመቻቸላቸውና እቅድ መያዙንም ቃል አቀባዩ ማስታወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ እህል ጭነው የሚጓጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሽብር ጥቃት በመፈጸም የእርዳታ መስመር እንዲዘጋ ማድረጉን የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ  ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መቐለ 2ኛውን በረራ እንደሚያደርግ መንግስት መግለጹም  ይታወቃል፡፡