የጉራጌ ልማትና ባህል ማኅበር በዞኑ የችግኝ ተከላ መርኃግብር አካሄደ

የጉራጌ ልማትና ባህል ማኅበር

ሐምሌ 17/2013 (ዋልታ) – የጉራጌ ልማትና ባህል ማኅበር በጉራጌ ዞን እንሞርና ኤነር ወረዳ ጋህራድ ቀበሌ የችግኝ ተከላ መርኃግብር አካሄደ፡፡

በተከላ መርኃግብሩ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች፣ የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞን ለማረጋገጥ የጉራጌ አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ገልጸው፣ ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን በጋራ መወጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እንደ ክልል አንድ ቢሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱንና ይህንን ለማሳካት የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብርን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሺሰማ ገ/ስላሴ በበኩላቸው፣ የችግኝ ተከላ ስራ ለዘጠኝ  ተከታታይ ጊዜ መደረጉን ገልጸው፣ የቀደምት አባቶችንን ፈልግ በመከተል ማህበሩ በጥናት ከለያቸው ጉዳዮች አንዱ የአፈር መሸርሸር እና የአየር ንብረት ለውጥ ነው ብለዋል።

በዘቢዳር ተራራ  አናት ላይ የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ስራ ዋና ዓላማው  ስለ አየር ንብረት ለውጥ አስፈለገውን ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ያሉ ሲሆን፣ የእያንዳንዱ አርሶ  አደር ቦታ በአረንጓዴ  አሻራ መሸፈን የፕሮግራሙ ግብ መሆኑን ተናግረዋል።

በተከለ ፕሮግራሙ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም የቡና ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ችግኞች እንዲያድጉ መንከባከብ አስፈላጊ እንደሆነና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማጠናቀቅ ሁሉም የማህበሩ አባልና ደጋፊ የበኩልን ማበርከት አለበት ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብርን ከማህበሩ ጋር በጋራ በመተግበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመነገባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮው ዓመት 117 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስከ አሁን 71.4 ሚሊየን መተከላቸውን ጠቁመው፣ ይህም የዞኑን የደን ሽፋን ለመሳደግ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።

መትከል ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ህብረተሰብ  የእንክብካቤ ስራ እያከናወነ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ በተከላው ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የእነምርና ኤነር ወረዳ ዋና አስተዳደር ያዕቆብ ግርማ የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ኘሮግራም ልዩ የሚያደርገው 6ኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቀን እየተከልን መገኘታችን ነው ብለዋል።

በተያዘው ክረምት በወረዳው 10 ሚሊየን የደን እና የቡና ችግኞችን ለመትከል ታሰቦ 6 ሚሊየን ተተክለዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ከጉራጌ ልማትና ባህል ማኅበር እና ከጉራጌ ዞን ጋር በመተባበር 15ሺህ የደን፣ የፍራፍሬና የቡና ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል፡፡

(በመሰረት አሰበ)