የሰሜን ሸዋ፣ ባሌና ጅማ ዞኖች ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 293 በሬዎችና 241 በጎችን አበረከቱ

የሰሜን ሸዋ፣ ባሌና ጅማ ዞኖች ነዋሪዎች

ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ፣ የባሌና ጅማ ዞን ነዋሪዎች በግንባር ወያኔን ለሚፋለመው የሀገር መከላከያ ሰራዊት 293 ሰንጋዎችና 241 በጎችን በድጋፍ አበረከቱ።

የዞኑቹ ነዋሪዎች ሰንጋና በጎቹን ያበረከቱት ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን በመግለጽ አሸባሪውን ህወሓት ባወገዙባቸው ሰልፎችና መከላከያ ሰራዊትን የተቀላቀሉ ወጣቶችን በሸኙባቸው ስነ ሥርዓት ላይ ነው።

የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ዛሬ ከወጣቶቹ ሽኝት ስነ ሥርዓት ጎን ለጎን 77 ሰንጋዎችና 201 ሙክት በጎችን ለመከላከያ ሰራዊት በድጋፍ አበርክተዋል።

በተመሳሳይ በባሌ ዞን የሮቤ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ካደረጉት የድጋፍ ሰልፍ በተጓኝ የሀገር ሉዓላዊነት አርማ ለሆነው የመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በራሳቸው ተነሳሽነት ለእርድ የሚውሉ 32 ሰንጋዎችን በመግዛት ድጋፍ አድርገዋል።

የጅማ ዞን ነዋሪዎችም ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በድጋፍ ሰልፍ ያሳዩ ሲሆን፣ ከሰልፉ ጎን ለጎን 184 ሰንጋዎችና 40 በጎችን ለግሰዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ነዋሪዎቹ በቀጣይ የሀገር መከታ ለሆነው መከላከያ ሰራዊት አጋርነታቸውን ለማሳየት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።