የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ህወሀት እየፈፀማቸው ያላቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን አወገዙ

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች

ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ህወሀት እየፈፀማቸው ያላቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን አወገዙ፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን፣ የጁንታው ህወሓት ቡድን ህፃናትን ለጦርነት የሚማግድ ዕኩይ ቡድን መሆኑ ታውቆ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።

ህፃናትንና ሴቶችን ለጦርነት እየማገደ ያለው ህወሓት በዚህ ስአት እያደረገ ባለው እኩይ ድርጊት ብቻ በአለም አቀፍ ህግ ሽብርተኛ መባል ያለበት ቡድን መሆኑን ሰልፈኞቹ ገልፀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመድ መሀመድ ቡህ ሰልፉ የተዘጋጀው ለመከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ለማሳየት መሆኑን ገልጸው፣ እኩይ ድርጊት እየፈፀመ ያለው ጅንታ ሊወገዝ ይገባዋል ብለዋል።

በስልፉ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከተማ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ ምዕራባውያን በእጅ አዙር የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ጠይቀው፣ ለአቅመ ጉልበት ያልደረሱ ህፃናትን ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን አሸባሪ ቡድን ለማስወገድ የትግራይ ወንድም ህዝብ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ስነሥርዓት ላይ ህፃናትና ታዳጊዎችን በመወከል ንግግር ያደረገችው ታዳጊ ሩት ታከለ የትግራይ ህፃናትና እንስቶች በጁንታው እየደረሰባቸው ካለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ልንታደጋቸው ይገባል ስትል መልዕክት አስተላልፋለች።

የድጋፍ ሰልፉ ታዳሚ የሆኑ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችም ከትግራይ ህዝብ ጋር ፀብ እንደሌላቸው በመግለፅ ንፁሀንን እያስጨረሰ ያለውን አሸባሪ ለማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን ሊቆም እንደሚገባው ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ በያዙት መፈክርና በአንደበታቸው “ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ ወደ ፊትም ታሸንፋለች”፤ “እኛ ድሬዎች ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ነን” ፤ “ክብርና ሞገስ ውድ ህይወታቸውን ለሰጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት”፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላማችንን በማስጠበቅ ልማታችንን እናረጋግጣለን” የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

በድሬዳዋ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በደምና አጥንቱ መስዋዕትነት ሀገርን እየጠበቀ ላለው ሰራዊት የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

(በደምሰው በነበሩ)