ባለፉት ሳምንታት ከ41 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሳቸው ተገለጸ

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – ባለፉት ሳምንታት 41 ሺህ 873 ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለያዩ ጉዳዮች ሳምናታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምክትል ዋና ፀሐፊነት የፖለቲካና የሰላም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ  ሮዝመር ዲካርሎ ጋር በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ እና በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በተመለከተ፡ ኢንቨስትመንት በዋሽንግተን ዲሲ NNPA Newswire ለተሰኘ ጋዜጣ ፣ በኩዌት አል-ራይ ጋዜጣ ፣በፓሪስ በቴሌኮም ዘርፍ የኢንቨስትመንት የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑንና ከአውስትራሊያ ፎረስት ኪውር ሜታልስ ግሩፕ የተባለ ኩባንያ በኢነርጂ ዘርፍ ለመሰማራት እና ከኩዌት አል በደር ከተባለ አለም አቀፍ ኩባንያ ጋር በግብርና ፣በኢነርጂ፣በማዕድን ፣በቴሌኮም፣ በነዳጅ፣በቱሪዝምና በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተው የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ተደርጓል ነው ያሉት።

በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት መካሄዱንና ክልላዊ እና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ለማምጣት የተመሰረተ እና ከነጻ ንግድ ቀጠና ወደ ፖለቲካ ውህደት ለማሸጋገር ግብ መጣሉ፤ የአፍሪካ የንግድ ድርሻ ከሌሎች አህጉራት አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን፣ የሚፈጥራቸው እድሎች፣ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና ሊያስከትል የሚችልባቸውን አሉታዊ ተጽእኖዎች ላይ ማብራሪያ መሰጠቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በአሜሪካን ሃገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተቋቋመው ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር አስተባባሪነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሃብት ለማሰባሰብና ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማሳየት ታላቅ የኢትዮጵያዊነት ትዕይንት በዋሽንግተን ዲሲ መካሄዱንና በወቅቱም ከ100ሺ ዶላር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን አንስተዋል።

በጃፓን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ውድድርን እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ጃፓን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት መደረጉን፣ በኬንያ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በአገራቸው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ እና በአገራ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡