የፕላንና ልማት ኮሚሽን በሸዋሮቢት ከተማ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር አካሄደ


ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) –
የኢፌዴሪ የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ከተጠሪ ተቋማቱ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በሸዋሮቢት ከተማ የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ ሉባባ መኮንን ሲሆኑ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የፕሮግራሙን ዓላማ በተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡
ዶክተር ፍጹም ኮሚሽኑ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያካሄዳቸውን የኢትዮጵያን እናልብሳት እና የበጎ ፍቃድ ተግባራትን አንስተው በሸዋሮቢት ከተማ ተገኝተው በዚሁ ተግባር ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደደር ከከተማው ትምህርት ቢሮ ጋር በአንድነት በመሆን ለት/ቤቶች የሚሰጡ ዋጋቸው 300 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ርክክብ ያካሄደ ሲሆን፣ የሮቢ (ዙጢ) የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በመገኘት ጉብኝት በማድረግ 300 ሺህ ብር የሚፈጅ ዕድሳት አስጀምረዋል፡፡
ከከተማው አስተዳደር አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ በጎ-አድራጎት ተቋማትና የወጣቶች በዚህ በጎ-ተግባሩ መሳተፋቸውን ከኮምሽኑ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።