አትሌት ደራርቱ ቱሉ በቶኪዮ በአትሌት ሰለሞን ባረጋ በተገኘው ድል የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላለፉ

 ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – በቶኪዮ ኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ውጤትን በማስመልከት የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳት አትሌት ደራርቱ ቱሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በጃፓኗ-የቶኪዮ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የአትሌቲክስ ውድድር በተጀመረበት እለት በ10000 ሜትር ወንዶች የፍፃሜ ውድድር በአትሌት ሰለሞን ባረጋ ለኢትዮጵያ ባመጣው የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያ እጅግ ደስ ብሎናል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቷ “ለመላው የሃገራችንን ህዝቦች በራሴና በኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚና ማኔጅመንት ኮሚቴ፣ አሰልጣኞች፣ ኦፊሻሎችና ሰራተኞች ስም እንኳን ደስ አለን እያልኩኝ ላለፉት ስምንት የዝግጅት ወራት ከጎናችን ለነበራችሁ በሙሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው፤ ድሉ ይቀጥላል” ሲሉ ነው በፌዴሬሽኑ ማህበራዊ ድረ ገፅ በኩል መልእክታቸውን ያስተላለፉት።
አትሌት ደራርቱ ቱሉ “የሃገራችንን ክብር በአትሌቲክሰ ጀግኖቻችን ገና ከፍ ይላል” ብለዋል።