በመዲዋ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 98 ሽጉጦች እና 6ሺህ ጥይት ተያዘ

ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 6ሺህ ጥይት እና 98 ሽጉጥ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተሽከርካሪው ከቦሌ ቡልቡላ ወደ ቦሌ ሚካኤል እየተጓዘ ወረዳ 05 ሚሊኒየም ፓርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርስ ነው በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅንጅት በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡
በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻም 58 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ፣ 1ሺህ 988 የብሬን፣1ሺህ 286 የክላሽ፣ 1ሺህ 576 የሽጉጥ እና 154 የሌሎች መሳሪያዎች ጥይቶች በማዳበሪያ ተጠቅልለው ተይዘዋል፡፡
ከተያዙት የሽጉጥ ጥይቶች መካከል የተወሰኑት በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት በብርበራ የተገኙ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም 1 ገጀራ፣ 2 ጩቤ፣ 2 የክላሽ ካርታ እና 1 ወታደራዊ ትጥቅ መያዣ ቀበቶ በፍተሻው መገኘታቸው ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ሐምሌ 14 ቀን አንድ ተሽከርካሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ሲደርስ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
በተሽከርካሪው ላይ በተደረገ ፍተሻም 40 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ እና 996 የብሬን ጥይት የኋላ ኮፈን ውስጥ ተደብቆ ተገኝቷል፡፡
በቁጥጥር ስር በዋሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮሚሽኑ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተሽከርካሪቸውን በውሰትም ሆነ በኪራይ ለሌላ ሰው አሳልፈው በሚሰጡበት ወቅት ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈፀምበት እንደሚችል በመገንዘብ አስፈላጊውን ክትትል እና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡