የጎጃም ፋኖ የሀገሩን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር አቀና


ሐምሌ 25/2013 (ዋልታ) –
የአሸባሪው የህውሀት ቡድን ኢትዮጵያን ለመበታተን የከፈተውን ጦርነት ለመመከትና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የፋኖ አባላት ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡
ለፋኖ አባላቱ በፍኖተ ሰላም ከተማ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡
“የአባቶቻችንን የአርበኝነትና የፋኖነትን ታሪክ በመድገም አሸባሪውን በመደምሰስ የሀገሪቱን ሰላም እናስጠብቃለን ” ያሉት አባላቱ የመንግሥትን የክተት ጥሪ ተቀብለው መዝመታቸውን ተናግረዋል፡፡
መቶ አለቃ አሰፋ አድማሱ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር እየዘመተ ያለው ፋኖ አባላት አስተባባሪ ናቸው፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሀገሪቱ እንድትበታተን እና ታላቋ ትግራይን ለመመስረት እየታተረ ነው ብለዋል፡፡ የፋኖ አባላትም ይህንን ቀድሞ ይረዳ ስለነበር የአሸባውን ትህነግ ሴራ ለመበጣጠስ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
“ፋኖነት ለኢትዮጵያ እና ለነጻነት መስዋእት መሆን ነው” ያሉት መቶ አለቃ አሰፋ መንግሥት ባቀረበው የክተት ጥሪ መሠረት በነፍስ ወከፍ ያለውን የግል መሳሪያ ይዞ ለእናት ሀገሩ መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
የፋኖ አባላቱ የመንግሥትን ጦር የሚመራው አካል በሚያሰማራው ግንባር በመሰለፍ ትህነግን ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የፋኖ አባላት የሽኝት መርኃ ግብር ላይ የሃይማኖት አባቶች ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ የፋኖ አባላት የመንግስትን ጥሪ ተቀብላችሁ ለመዝመት መወሠናችሁ ለሀገራችሁ ነጻነት የምትከፍሉት መስዋእትነት ስለሆነ ደስ ሊላችሁ ይገባል ያሉት የፈለገ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ መጋቢ ብሉይ አባ አብርሃም ደጉ ናቸው፡፡
የቀድሞ አባት አርበኞች በሀገር ላይ የተቃጣን ጥቃት ለመከላከል ታቦት ይዘው መዝመታቸውን ያስታወሱት መጋቢ ብሉይ አባ አብርሃም “እናንተም ቡራኬ ተቀብላችሁ ጸሎት ተደርጎላችሁ ወደ ግንባር መዝመታችሁ ለእናት ሀገራችሁ ያላችሁን ፍቅር ያሳያል” ብለዋል፡፡
መጋቢ ብሉይ አባ አብርሃም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለፋኖ አባላት በአደራ አስረክበዋል ያለው አሚኮ ነው፡፡