ሚኒስቴሩ ለመቄዶኒያ ያገለገሉ የግንባታ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

ሐምሌ 26/2013 (ዋልታ) – የገቢዎች ሚኒስቴር መቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ማህበር ዜጎችን ከጎዳና ለማንሳት ለሚያከናውነው የማስፋፊያ ስራ የሚያግዝ ያገለገሉ የግንባታ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው “የህዝብን ሃብት ለህዝብ” እና “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል ሃሳብ  ልዩ ልዩ ድጋፎች መደረጉን ገልጸው መቄዶንያ  የዜጎችን ሸክም ለማቃለል የሚሰራ ተቋም በመሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴር ከሚሰራው ስራ ጋር የሚደጋገፍ ስራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የተቋማዊ አቅምና ድጋፍ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ከመደበኛ ስራችን ጎን ለጎን ድጋፍ የሚያሻቸው ዜጎችን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል፡፡

የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ቢኒያም በለጠ  ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ተጨማሪ ተረጅዎችን ለመርዳት በአዲስ አበባ እና በክልሎች ለሚያከናውነው የማስፋፊያ ፕሮጀክት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ ግምቱ አንድ ሚሊየን 226 ሺህ 555 ብር ሲሆን በዕቃዎች ዓይነት የአልሙኒም ፓርቲሽን፣ የአልሙኒየም መስኮት፣ በሮች፣ የባኞ ቤት ዕቃዎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡