የጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው

ሐምሌ 26/2013 (ዋልታ) – “ጡት ማጥባትን መጠበቅ የጋራ ሀላፊነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከሀምሌ 25 እስከ ነሀሴ 1/2013 ዓ.ም ድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የጡት ማጥባት ሳምንትን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደ ዓለም ሆነ ኢትዮጵያ የህጻናት መቀንጨር አሳሳቢ መሆኑን አንስተው መቀንጨርን ለመከላከል በዋናነት ጡት ማጥባት ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአለም 21 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት የቀነጨሩ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ከሳህራ በታች ባሉ ሀገራት ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ 37 በመቶ ህጻናት መቀንጨራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የቀነጨሩ ህጻናት በቀላሉ ለበሽታ ከመጋለጣቸው በተጨማሪ ትምህርት መቀበል አለመቻልና በርካታ ችግሮችን ያስከትልባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ ይህን ተከትሎም ኢኮኖሚያዊ ችግር ያስከትላል ብለዋል፡፡

ልጆች ከተወለዱ በአንድ ሺህ ቀናት ወይም እስከ ሁለት ዓመት የተመጣጠነ ምግብ መመገባቸው ለዘላቂ ጤንነታቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ተገልጿል፡፡

ህጻናት ከተወለዱ እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት መጥባታቸው ደግሞ ለህጻናቱም ጤና ሆነ ለእናት ትልቅ ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ጡት ማጥባት ለእናቶች የጡትና የማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭነትንም እንደሚቀንስም ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ መልካም የሚባል ጡት የማጥባት ልምድ እንዳለ የገለጹት ዶክተር ሊያ 97 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ጡት የሚያጠቡ ሲሆን ነገር ግን እስከ ስድስት ወር የሚያጠቡት 59 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ናቸው ብለዋል፡፡

(በመስከረም ቸርነት)