ሐምሌ 29/2013(ዋልታ) – አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት በሚል መሪ ቃል በተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገባውን ደለል ለመከላከል ያላቸውን ሚና በተመለከተ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው ::
አውደ ጥናቱ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ አስተባባሪ ድ/ቤት በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ነው።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ አውደ ጥናት ዩኒቨርሲቲዎች በዋናነት በግድቡ ላይ የሚፈጠርን ደለል ለመከላከል የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
በዚህ የአውደ ጥናት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ብሔራዊ አስተባባሪ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዶይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በ2013 በጀት አመት 2 ቢሊዮን 49 ሚሊዮን ብር ለግድቡ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡
ላለፉት 10 አመታት የግድቡን ስራ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ኢትዮጵያ ከእለት ጉርሱ በመቀነስ አስተዋፆ በማድረጉ ግድቡ አሁን ላይ 81 በመቶ ለመድረስ ችሏል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ትልቅ ስራ ከፈታችን ይጠብቀናል ብለዋል ::
ስለሆነም በተፋሰሱ አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ግድቡን ከደለል ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ የደለል መከላከል ስራ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት ::
ዶ/ር አረጋዊ አክለውም ጐን ለጐን ደለሉን የመከላከል ስራ ብቻ ሳይሆን ታጥቦ የሚሄደውን ለም አፈር መከላከል የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል::
የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚረዳውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኘ የመትከል እና የመንከባከብ ስራ ላይ ትኩረት እናድርግ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግድብ ከሚለው ፅንሰ ሀሣብ የዘለለ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል ::
አክለውም ኢትዮጵያ በአድዋ ድል እንደተቀዳጀች ሁሉ በህዳሴ ግድብም በኢኮኖሚ እና በሀይል አቅርቦት ድል የምትቀዳጅበት ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡:
በመሆኑም ይህን ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከደለል ለመከላከል የሚያስችል በጥናት ላይ የተደገፈ ስራ በገራ ለመስራት በተፋሰሱ የሚገኙ 10 ዩኒቨርስቲዎች ስምምነት ያደርጋሉ ብለዋል።
የአውደ ጥናት መድረኩ ለሁለት ቀናት ዛሬ እና ነገ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
(በሜሮን መስፍን)