የሰልጣኞች ቅበላ ለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ሚና ያላቸው የክህሎት ዓይነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ይሆናል ተባለ

ሐምሌ 30/2013 (ዋልታ) – ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፣የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ የ2014 እቅድ ስልጠናዊ ግምገማ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ዘርፉ ለአገራዊ እድገት እና ብልጽግና ያለዉን አስተዋጾ “የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና እና ሥራ ዕድል/ባለፀጋነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸዉ” በማለት ቁልፍ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት መሆኑን በተግባር የሚያመላክቱ ውጤቶች ቢኖሩም፣ ለመስኩ የተሰጠው ትኩረት ደካማ ሆኖ በመቆየቱ እንደዘርፍ ማበርከት የሚችልዉን አስተዋጾ በሙሉ አቅም መጠቀም አልተቻለም ያሉት ሚኒስትሩ በ2013 አፈጻጸም ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር የተሰሩ ተጨባጭ ስራዎች ጥሩ ጅምሮች በመሆናቸዉ በቀጣይም ተጠናክረዉ ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሳሙኤል አክለዉም በ2014 በጀት ዓመት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ዉጤታማ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱን እና የስልጠና ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ ለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን የክህሎት ዓይነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የሰልጣኝ ቅበላ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
ዘርፉን በእዉቀት ሊመራ የሚችል የስራ አመራር ቦርድ በማዋቀር፣ አመራሮችን በመመደብ ፣ተቋማትን እና የስልጠና ጥራትን መለኪያ ስታንዳርድ በማዉጣት ተወዳዳሪ፣በቂ እና የበቃ የሰዉ ሀይል ለማፍራት በትኩረት መሰራት እንደሚገባም አሳስበዋል ሚኒስትሩ፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የፌዴራልና የክልል የቴክኒክና ሙያ አመራሮች፣ 81 የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲኖችና ሎሎችም እየተሳተፉ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡