የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ለ2014 14 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ

ነሀሴ 01/2013 (ዋልታ) – የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ለ2014 የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ የቀረበለትን 14 ቢሊዮን 70 ሚሊዮን ብር በጀት አጸደቀ።
ይህም ከባለፈው አመት በጀት ጋር ሲነፃፀር የ16 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል።
በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ከጸደቀው በጀት 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከፌደራል መንግሥት በድጎማ የሚገኝ ሲሆን፣ክልሉ አራት ቢሊዮን ብር ከውስጥ ገቢ በማሰባሰብ እንደሚሸፈን ተመልክቷል።
ቀሪው ከውጭ በሚገኝ ድጋፍ እንደሆነ የምክር ቤቱ የፋይናንስና በጀት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘነበ ዘርፉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ የምርጫ ዘመን አንደኛ አመት የስራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ ምክር ለሶስት ቀናት በነበረው ቆይታ የ2013 የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን የገመገመ ሲሆን በተጨማሪም የምክር ቤቱን ሪፖርት፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ስራ አፈፃፀምንም መገምገሙን የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ሠለሞን ላሌ ገልፀዋል።
የክልሉ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አራርሶ ገረሙ በበኩላቸው፤ በጀቱ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ግብዓቶችን ለማቅረብና ተቋማትን ለማደራጀት ጭምር ያመላከተ መሆኑን አብራርተዋል።
በጀቱ በክልሉ ለዘላቂ የልማት ግቦች ፣ ለደመወዝና ሌሎች አስተዳደራዊ ተግባራት ማስፈጸሚያ እንዲውል የቀረበ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የመንግሥት አገልግሎት ለማቀላጠፍ ለዞን ማቋቋሚያና መጠባበቂያም በበጀቱ ተካቷል።
በጀት አመቱ በክልሉ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ነባር የመንገድ፤የውሃና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ ማከናወን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የሲዳማ ክልል አዲስ እንደመሆኑ የመንግሥት ውስን ሀብት ሳይባክን ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና በተለይ ግብርናውን በማዘመን የመስኖ ልማትና ለአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ትኩረት በመስጠት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችል ክልል ሆኖ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምክርቤቱ በመጨረሻ ቀን ዉሎው የኦዲት፣የጠቅላይ አቃቤ ህግ እና የፀረሙስና ቢሮዎችን የ2013 አፈፃፀም በመገምገም እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል።