በአንድ መድረክ ከ140 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ተሰበሰበ

ነሐሴ 03/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በአንድ መድረክ ከ140 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

ከምሽቱ 10 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት በዘለቀው የኢትዮጵያውያን የዳላስ አብሮነት ምሽት የአጋርነት መልዕክቶችን በማስተላለፍ በኢትዮጵያ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ መሰብሰቡን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

አምባሳደሩ በዚህ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ አዲስ ክብረ ወሰን መመዝገቡንም ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ እንዲገኝ ላስተባበሩ የኮሚቴው ሰብሳቢና አመራሮች፣ ለኃይማኖት አባቶች፣ ለመድረክ መሪዎች እንዲሁም በጨረታ ጭምር በተደጋጋሚ የለገሱ አካላትን አመስግነዋል አምባሳደሩ ፡፡

በቀጣይ በዳላስ የሚኖሩ ወገኖችን ፈለግ በመከተል በሌሎችም ከተሞች የተጠናከረ የአጋርነትና የልገሳ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡