የቱሪዝም ኢትዮጵያ ሰራተኞች ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒዬም ህክምና ኮሌጅ ሰራተኞች ጋር በአንኮበር ችግኝ ተከሉ

አንኮበር ነሐሴ 03/2013 (ዋልታ) – የቱሪዝም ኢትዮጵያ ሰራተኞች ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒዬም ህክምና ኮሌጅ ሰራተኞች ጋር በመሆን በአንኮበር የችግኝ  ተከላ መርሃግብር ከወኑ።

በአንኮበር ቤተመንግስት ቱሪዝም ኢትዮጵያ እና የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒዬም ህክምና ኮሌጅ ባለሙያዎች ችግኝ የተከሉ ሲሆን  ለጤናማ ህይወት በሚልም ደብረ ብርሃን መግቢያ ላይ 3 ኪ.ሜ የእግር ጉዞ አድርገዋል

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ግርማ “ችግኝ ተከላ ዋነኛው የቱሪዝም ደጋፊ ተግባር ነው” ብለዋል።

“የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲለሙ ከተፈለግ ስነምህዳሩን መጠበቅ ትልቁ ሃላፊነት ነው” ሲሉ አክለዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ማነቆ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ዛሬም ድረስ ፈታኝ ሆኖ ቢዘልቅም የቱሪስት መዳረሻዎች ከኮሮና ነጻ በሆነ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ፊት ለፊት ሆነው ሲታገሉ ለነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ትልቅ ምስጋና እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒዬም ህክምና ኮሌጅን በመወከል በችግኝ ተከላ እና ጉብኝት  የተሳተፉ ሃኪሞች በበኩላቸው  ተገቢውን የኮሮና ቫይረስ የጥንቃቄ መንገድ በተከተለ መልኩ የጉብኝት ባህል እንዲዳብር እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲስፋፋ  መልዕክት አስተላልፈዋል።

(በእንየው ቢሆነኝ)