ህወሓት እየፈጸመ ያለውን ወረራ በአንድነት መመከትና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

ነሃሴ 3/2013(ዋልታ) – በአፋር እና በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በአሸባሪው ሃይል እየተካሄደ ያለው ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያን ሁሉም በአንድነት ሊመክተው እና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያን መታደግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን የተመራ የፌዴራልና የክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችንና የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ በጋይንት ጨጨኾ አቅጣጫ በመቄት ወረዳ ደብረ~ዘቢጥ አካባቢ የመስክ ጉብኝት አካሄዷል።

በጋይንት ጨጨኾ አቅጣጫ በመቄት ወረዳ ደብረ~ዘቢጥ አካባቢ ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያ እያካሄደ ያለውን የአሸባሪ ሃይል ለመመከት የተሰለፈውን የመከላከያ ሰራዊት፣ የልዩ ሃይል፣ የሚሊሻና የፋኖ አደረጃጀት እንቅስቃሴ ተመልክቷል።

የአሸባሪውን ሃይል እኩይ እንቅስቃሴ እና ድርጊት ለመመከት ከጋይንት ጀምሮ የአከባቢው ማህበረሰብ በከፍተኛ ወኔና ቁርጠኝነት የሚያደርገውን ጠንካራ ዝግጅት ቡድኑ ለመታዘብ ችሏል።

በየአከባቢው የሚገኘው ማህበረሰብ ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከልዩ ሃይሉ፣ ከሚሊሻ እና ከፋኖ ጋር በመቀናጀት ሃገርን የመታደግ ታሪካዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ዝግጅት የሚያስደንቅ መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

የአከባቢው ማህበረሰብ ለሰራዊቱ፣ ለልዩ ሃይሉ፣ ለሚሊሻው እና ለፋኖ አደረጃጀት ጠንካራ ደጀንነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን በጉብኝቱ መታዘብ መቻላቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።