ሀገር የማፈራረስ ምኞትና የውጭ ኃይሎችን ለመመከት ሕዝቡ በአንድነት መቆም አለበት – አቶ ታገሰ ጫፎ

ነሀሴ 4/2013 (ዋልታ) –  የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የባንዳዎችን ሀገር የማፈራረስ ምኞትና የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ለመመከት ሕዝቡ በአንድነት መቆም እንዳለበት አሳሰቡ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ ደም ለግሰዋል፡፡

አፈ ጉባኤው ኢትዮጵያ የሌሎችን ሀገሮች ጥቅም ያለአግባብ መውሰድ እንደማትፈልግ ሁሉ የራሷንም ጥቅም አሳልፋ እንደማትሰጥ አውቀው የውጭ ወራሪ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል፡፡

አክለውም ወራሪውን ኃይል ለመመከት በትናንትናው ዕለት የምክር ቤት አባላትና የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ የለገሱ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የምክር ቤት አባላት ደማቸውን እየለገሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤት አባላትም ስንቅ በማዘጋጀት ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሰለፋቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነኢማ መሐመድ በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊቱ ሀገሩን ክብር ለመጠበቅ፣ የውጭ ወራሪዎችን ምኞት ለመግታትና ሀገር ለማፈራረስ የሚመኙትን የሀገር ውስጥ ጠላቶች ለመመከት መተኪያ የሌላትን ሕይወቱን ለመስጠት በግንባር ከተሰለፈው የመከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፋቸውን ለማሳየት ደም ለመለገስ እንደተነሳሱ ተናግረዋል፡፡