ከአምስት ሺህ በላይ የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – የምዕራብ ዕዝ ደጀን ጥበቃ ለሽብር ቡድኑ ሊደርስ የነበረ ከአምስት ሺህ በላይ የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር አዋለ።

የምዕራብ ዕዝ ዘመቻ ሃይል ክትትል ተወካይ ሻለቃ ጌታቸው ዋሬ እንዳሉት፣ ጥይቱ በሁለት ቋጠሮ ተደርጎ በአህያ ተጭኖ  ለሽብር ቡድኑ ሊደርስ ሲል ጫካ ውስጥ እንደተያዘ ጠቁመዋል።

ጥይቱ ወደ ቡድኑ ቢደርስ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ይሆን እንደነበር መጠቆማቸውን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሽብር ቡድኑ የሚያገኛቸውን ሎጀስቲካዊም ይሁን ሌሎች ድጋፎች ተከታትሎ ባልታሰበ ጊዜ በቁጥጥር ስር ማድረግ ቡድኑን የበለጠ ያዳክመዋል ያሉት ተወካዩ ፣ሰራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ ያልተቋረጠ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ጥይቱን በቁጥጥር ስር ካዋሉት የምዕራብ ዕዝ ደጀን ጥበቃ አባላት መካከል ሃምሳ አለቃ አብዲ ዓሜ እና ሃምሳ አለቃ ዮሀንስ ባይከዳ እንዳሉት፣ ጥይቱ በተላላኪዎች በኩል ሊደርስ እንደነበርና በትኩረትና በጥንቃቄ በማሰስና በመፈተሽ በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት ተናግረዋል።