በኒውዮርክ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያ ለህዳሴው ግድብ ከ62 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ነሃሴ 6/2013 (ዋልታ) – በአሜሪካ ኒውዮርክ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ62 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በዌብናር ባካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ ነው ድጋፉ የተገኘው።
በእንግድነት የታደሙት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው የግድቡን ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማድረግ በሁለት ዙር የተደረገው ሙከራ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ድጋፍ ጭምር መምከኑን አስታውቀዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ አነቃቂ ንግግር ያደረገው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሽቱ ሀገራችን ላይ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ችግር መነሻው ከአባይ ውሀ ጋር የተያያዘ በመሆኑ መፍትሄው ሁላችንም ተደጋግፈን ልንቆም ይገባል ብለዋል።
የፕሮግራሙ አዘጋጆች ለወደፊቱም የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ በማጠናከር የበኩላቸውን ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።