የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ ለማስጀመር ከተቋራጮች ጋር ቦታ ተረካከበ

ነሃሴ 6/2013(ዋልታ) – በ285 ሚሊየን ብር በጀት የ6 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ ለማስጀመር ከተቋራጮች ጋር የቦታ ርክክብ ማድረጉን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የመንገድ ግንባታው ለከተማዋ ልማት መፋጠን ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተጠቁሟል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረ መስቀል በዚሁ ወቅት እንዳሉት በከተማው በሦስቱም ክፍለ ከተሞች በ285 ሚሊየን ብር ወጪ የተለዋጭ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ለመገንባት ከሁለት አገር በቀል ተቋራጮች ጋር የቦታ ርክክብ ተደርጓል።

ከተማ አስተደሩ በአዲስ ክፍለ ከተማ ከዱባይ ካፌ እስከ ኤደን ገነት አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር በበኩር ክፍለ ከተማ ከሰባት ቤት ማዞሪያ ኮንዶሚኒየም እስከ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሶስት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ከጉብሬ አደባባይ እስከ ሉቄ ማዞሪያ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር በአጠቃላይ ስድስት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ተለዋጭ የአስፋልት መንገድ ስራ ለመስራት ለሁለት አገር በቀል ተቋራጮች ማስረከቡን አቶ እንዳለ ገልጸዋል።

ከተማዋ መልማት በሚገባት ልክ አለመልማቷን የገለጹት አቶ እንዳለ የሚጀመሩት የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ በከተማዋ ልማት ላይ ተጨማሪ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ጠቁመዋል።

በግንባታ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ከከተማው ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የከተማዋን እድገት ለማፋጠን አስተዳደሩ ሰፊ ጥረት እንደሚያደርግም ከንቲባው አክለዋል።

የከተማዋ የዘመናት ጥያቄዎች በለውጡ መንግስት ምላሽ እየተሰጠ ነው ያሉት የወልቂጤ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሄኖክ አብዱልሰመድ ናቸው።

እስከዛሬ ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፍ አንድ የአስፋልት መንገድ ብቻ እንደነበርና በዚህ ወቅት ከአንድ ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር በላይ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ በማንሳት አሁን ላይ ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ደግሞ ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ባለሀብቱ ወደ ከተማዋ ገብቶ እንዳያለማ የተለያዩ ጫናዎች ይደረግበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሄኖክ አሁን ላይ ግን ችግሩ ተቀርፎ ለባለሀብቱ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመላክተዋል።

በቀጣይም ስለ አጠቃላይ አሁናዊ የከተማዋ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ከጉብሬ አደባባይ እስከ ሉቄ ማዞሪያና ከማራኪ ካፌ እስከ ኤደን ገነት ያለው የሶስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ዛፍራን ትሬዲንግ የተሰኘው ተቋራጭ በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ የሚያጠናቅቀው ሲሆን ከሰባት ቤት ማዞሪያ እስከ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ያለው የሶስት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ በአበባው ሰለሞን ስራ ኮንስትራክሽን በሁለት ዓመት ተኩል የጊዜ ገደብ ገንብተው እንደሚያጠናቅቁ ተቋራጮቹ ተናግዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በኩል መሠራት ያለባቸው እንደ ወሰን ማስከበር እና ሌሎች ስራዎችን ከተከናወኑ ስራው ከተያዘለት ጊዜ ገደብ አስቀድመው ለመጨረስ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተቋራጮቹ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ዘይነብ አወል በከተማው የአዲስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ አቶ ነስሩ መሐመድ ደግሞ የጉብሬ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ በሰጡት አስተያየትም ከተማ አስተዳደሩ በአካባቢያቸው ያለው የመንገድ ችግር ከግምት በማስገባት ደረጃውን የጠበቀ ስራ ለመስራት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ከማህበረሰቡ የሚፈልገውን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።