መኢአድ ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

ነሃሴ 06/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አስታወቀ።

መኢአድ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እያደረሰ ያለውን ሀገር የማተራመስና የሽብር ተግባር አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ካለው ሀገር የማተራመስና የሽብር ተግባር ለመታደግ አባሎቹንና ደጋፊዎቹ ከመከላከያ ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ ናቸው ብሏል።

የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ደም በመለገስ ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል፤ ድጋፋቸውንም አጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል የፓርቲው መግለጫ።

ፓርቲው አሸባሪው ህወሓት ለ30 ዓመታት ሲያካሂደው የነበረውን የከፋፈለህ ግዛ ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ሲታገል መቆየቱንም አስታውሷል።

መኢአድ የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል የፖለቲካ አጀንዳዎቹን በይደር ይዞ የአገር አድን ትግሉን በይፋ መቀላቀሉን አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።