የኦሮሚያ፣ የጋምቤላ እና የቤንሻንጉል ጉመዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ተወያዩ

ነሃሴ 7/2013 (ዋልታ) – የኦሮሚያ፣ የጋምቤላ እና የቤንሻንጉል ጉመዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በጋራ የልማት እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡
በዉይይቱ ሶስቱ ክልሎች በምዕራብ ኢትዮጵያ የህዝቦችን ወድማማቸነት ለማጠናከር፣ የጋራ ልማት እና ጸጥታን ለማረጋገጥ አቅደዉ እየሰሩ መሆኑና እስካሁን ባለዉ ሂደትም አበረታች ለውጦች መመዝገብ መጀመራቸዉ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የህዝቦችን ጥቅም ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸዉ እና የፀጥታ ሁኔታ ላይም አንጻራዊ መሻሻሎች እየመጣ እንዳለ ገምግመዋል፡፡
በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በሌላ በኩል አመራሮቹ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና የምዕራብ ኢትዮጵያን ፀጥታ በተመለከተ በመወያየት ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በጁንታዉ ተላላኪዎችና የጠላት ሰርጎ ገቦች ላይ የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ የአከባቢዉን ሰላም ለማረጋገጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
በውይይት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታና ሌሎች የክልሎች እና የፌዴራል መንግስት የፀጥታ አካላት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡