የሚሰጣቸውን ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በሁመራ ግንባር የተሰማሩ የጸጥታ አባላት ገለጹ

ነሐሴ 10/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያን ሰላም ውሎ ሰላም ማደር የማይመኙት አሸባሪ ቡድኖች ከውስጥ እና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመናበብ የሕልውና ስጋት ከፈጠሩ ውለው አድረዋል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ አባላት “እኛ የማንመራት ኢትዮጵያ ትበጣጠስ” በሚል አጉል ብሂል ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስትራቴጂክ ጠላቶች እና ወራሪዎች ጋር የጅብ ጋብቻ ፈጥረዋል፡፡
ምዕራባውያን ደግሞ ሚዜዎች ሆነው በኢትዮጵያውያን ደም ለመድመቅ ከፍ እና ዝቅ ሲሉ እየተስተዋሉ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሕልውና ዘመቻውን ተቀላቅለው አኩሪ ገድል እየፈጸሙ ነው፡፡
በሁመራ ግንባር የተሰማሩት የጸጥታ አባላትም መንግሥት የሚሰጣቸውን ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን በተለይም ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት አባል በላቸው ወርቁ አሸባሪው ትህነግ በሀገር ላይ የፈጸመውን ክህደት ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ወቅቱ አሁን መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያን መለወጥ ከማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር ለሚሠራው አሸባሪው ትህነግ ከዚህ በላይ ትዕግስት በራስ ዜጎች ላይ እንደመፍረድ ስለሚቆጠር የማያዳግም ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ብሏል፤ ለዚህም እርሱ እና ጓደኞቹ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጸው፡፡
በሁመራ ግንባር ከተሰማራው የአማራ ልዩ ኃይል አባል ኮንስታብል በትሃ ነጋልኝ አሸባሪውን ቡድን በማያዳግም መልኩ ለመደምሰስ የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ተናግራለች፡፡
ኮንስታብል በትሃ ሕዝቡ ለሠራዊቱ የሚያደርገው የትጥቅ እና ስንቅ ድጋፍ ተጨማሪ ኃይል እንደሆናቸው ነው የተናገረችው፡፡
መንግሥት ካሳለፈው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በኋላ አሸባሪው ትህነግ በሁመራ ግንባር በተደጋጋሚ ውጊያ ፈጽሞ እንደነበር ሌላው የአማራ ልዩ ኃይል አባል መኮንን ንጉሴ ነግሮናል፡፡
የጸጥታ አካሉ በተቀናጀ መንገድ እርምጃ ወሰዶ አሸባሪ ቡድኑ ዳግም እንዳይሞክር ተደርጓል ብሏል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በሞራል፣ በኃይል እና በሎጀስቲክስ በተዳከመበት በዚህ ወቅት ቀርቶ ቀድሞውንም ፊት ለፊት የመግጠም ወኔውና ድፍረቱ እንደሌለው ለአሚኮ ገልጿል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን አባላት ከጥንት እስከ ዛሬ የተካኑት ሴራ እና ክህደት መሆኑን የገለጸው መኮንን አሁን ሁሉም ስለነቃባቸው ተገቢ ምላሽ እየሰጣቸው መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ኮቴያቸው ባልደረሰበት አካባቢ ሳይቀር “ተቆጣጥረነዋል” ማለት የወራሪው ትህነግ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ጦርነት ነው፤ ይህንንም ቀድሞ መረዳት እና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው ብሏል፡፡