ነሀሴ 12/2013 (ዋልታ) – ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትላንትናው ዕለት በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸውን በቦታው ተገኝተው አፅናንተዋል።
በትላንትናው ዕለት ከሰዓት በኃላ በጣለው ከባድ ዝናብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት መካኒሳ በሚገኘው መካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ቅጥር ግቢ እና በሌሎች አካባቢዎች በደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከልብ ማዘናቸውን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ ከማጽናናት ባለፈ ተጎጂዎችን የማቋቋም እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ እና የውሃ ተፋሰስ ስፍራዎችን የማጽዳት ስራ ለማከናውን እና የጎርፍ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበበ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍሰሃ በበኩላቸው ትላንት ከእኩለ ቀን ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በህይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እስካሁንም በጎርፍ አደጋው የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና አጠቃላይ በህይወት እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በቀጣይ ይፋ እንደሚደርግ ኮሚሽነሩ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፐሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምክትል ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ጋር በመሆን በጎርፍ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች በቦታው በመገኘት አፅናንተዋል።