ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል ወደ ገበያ ሊያቀርቡ በነበሩ ድርጀቶች ላይ እረምጃ ተወሰደ

ነሀሴ 12/2013 (ዋልታ) –ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል እና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን ወደ ገበያ ሊያቀርቡ በነበሩ 40 ሺህ 185 ድርጀቶች ላይ እረምጃ መወሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ከምርት ጥራት ቁጥጥር አንጻር የኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ሥራዎችን በማካሄድ የሸማቹን ህብረተሰብ ጤንነት፣ ደህንነት፣ የአካባቢ ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ በፌዴራል እና በየደረጃው ባለዉ የንግድ መዋቅር በተከናውኑ ዋና ዋና ስራዎች በሕገ ወጥ ድርጊት በፈጸሙ ደርጀቶች ላይ እረምጃ መውሰድ ተችሏል፡፡

እርምጃ የተወሰደው የንግድ ስርዓቱን በመጣስ የህዝብን ጤናና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ፈጽመዋል ባላቸው ድርጅቶች ላይ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ዋና ዋና የምርት ክለሳ ወይም ባዕድ ነገር መቀላቅል እና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት የምርት አይነቶች መካካል ቅቤ 5008 ኪ/ግ፣ በርበሬ 234.4 ኩ/ል፣ አይብ 78 ኪ/ግ፣ ማር 585 ኪ/ግ፣ ዱቄት 13 ኩ/ል፣ እና ከበርበሬ ጋር ሊደባለቅ የተዘጋጀ ግማሽ መጋዘን ቀይ አፈር በፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲታይ ተደርጓል፡፡

የገበያ ቦታዎች በተደረገው የገበያ ኢንስፔክሽን ስራ መሰረት ዋና ዋና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት የሚታይባቸው ምርቶች መካከል ዱቄት 50 ኩንታል የነቀዘ እና የተላ ዱቄት ከበቆሎ ዱቄት ጋር ለመቀላቀል የተዘጋጀ፣ 500 ደርዘን የፕላስቲክ ለስላሳ መጠጥ ግዜ ያለፈበት ይገኙበታል፡፡