ህወሃት ሂሳቡን ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር እንጂ ከአማራ ጋር ብቻ አያወራርድም – አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ

ነሀሴ 12/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሃት ሂሳቡን ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር እንጂ ከአማራ ጋር ብቻ እንደማያወራርድ የሶማሊ ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳደር ሙስጠፋ ሙሁመድ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ እና ሌሎች አመራሮች ከተለያዩ ቢሮዎች የተወጣጡ በክልል ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ሰራተኞች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች፣ በመንግሥት ሰራተኞች ኑሮ መሻሻልና ጥቅማጥም፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ ያተኮረ ነው፡፡

ምክትል ርዕሰ መሰተዳደር ሙስጠፋ ሙሁመድ ሰራተኞች ያለ ፍርሃት እና መሸማቀቅ ችግሮችንና ያሉትን ትችቶችን እንዲያቀርቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሰራተኞችም እንደ መንግሥት ሰራተኛነት ያለባቸውን ችግሮች፣ በፍጆታ እቃዎች እና በኑሮ ውድነት፣ ከመስሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ በሰራተኞች ምደባና ደሞዝ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን አንስተዋል።

ምክትል ርዕሰ መሰተዳደሩ ከለውጡ በኋላ በሶማሊ ክልል ሁለንተናዊ ለውጥ እንደመጣና ክልሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰላም በመኖር ላይ እንደሆነ ገልፀው፣ ዜጎች በክልሉ እኩል የስራ እድል የማግኘት መብት አላቸው ብለዋል።

አክለውም በሶማሊ ክልል ማንም ሰው በብሄሩና በአመለካከቱ ችግር እንደማይደርስበትና ለህግ ተገዥ ሆኖ ሃሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

ህወሃት በፕሮፓጋንዳ ሀገር የማፍረስ አቅም እንደሌለውና በፕሮፓጋንዳ መልክ ከአማራ ጋር ብቻ አወራርዳለው የሚለው ሂሳብ እንደሌለና ሂሳቡን የሚያወራረደው ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ነው ብለዋል፡፡

ከአሸባሪ ህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች የክልሉ መንግሥት ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ማለታቸውን ከሶማሊ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሶማሊ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር አብዲ በክልሉ የመንግሥት ሰራተኞች ያሚያነሱት ጥያቄዎች መፍትሔ እያገኙ እንደሆነና፣ ሁሉም በደረጃውና በተማረው መሰረት እየተመደበ መሆኑን ገልጸው የሰራተኛው ኑሮ የበለጠ ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል፡፡