ፍተሻ ጣቢያው የንግድ ትስስር እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ

ነሃሴ 13/2013 (ዋልታ) – የሞያሌ የጋራ ፍተሻ ጣቢያ  የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር ፣ የሀገራቱ  የንግድ ትስስር እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቆ የተከፈተው የኢትዮጵያ እና የኬንያ የሞያሌ የጋራ ፍተሻ ጣቢያ የንግዱ ማህበረሰብ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ በር የከፈተ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ትስስርም እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ተብሏል፡፡

የሞያሌ የጋራ ፍተሻ  ጣቢያ፤ አገልግሎቱን በይፋ መስጠት ከጀመረ በኋላ የታዩ ስኬቶች እና ያጋጠሙ እንቅፋቶችን የሚዳስስ ውይይት የሁለቱ ሀገራት የጉምሩክ አመራሮች፣ ነጋዴዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች  በተገኙበት ምክክር ተደርጓል፡፡

በጉምሩክ ኮሚሽን የአለም አቀፍ ትብብር አጋርነት የስራ ሂደት አስተባባሪ አብርሐም ጉደታ የሞያሌ የጋራ ፍተሻ ጣቢያ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተቀናጀ የጉምሩክ እቃ አወጣጥ እንዲኖር በማስቻሉ የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

የተቀናጀ የድንበር አገልግሎት አዲስ የጉምሩክ ጽንሰ ሀሳብ  መሆኑን የጠቆሙት  አቶ አብርሐም ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ለማሳለጥ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በፊት በመግቢያ እና መውጫ በሮች ይካሄድ የነበረው ተደጋጋሚ  የእቃ ፍተሻን ያስቀረ በመሆኑም የደንበኞችን እንግልት በመቀነስ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኬንያ ሞያሌ የተቀናጀ የድንበር አገልግሎት ሃላፊ  ጆይል ኢንደጌ በበኩላቸው የሞያሌ የጋራ የፍተሻ ጣቢያ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ያስቀረ ሲሆን የአካባቢውን ሰላም በማስፈን ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም የአገልግሎቱ መጀመር ከዚህ በፊት የነበረውን የተንዛዛ  አሰራር በማስቀረቱ በቅንጅት ችግር ምክንያት ይባክን የነበረውን ጊዜ እና ወጭ የቀነሰ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡