ለአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያስተላልፉ የሞከሩ 57 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ነሃሴ 13/2013 (ዋልታ) – ለአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያስተላልፉና ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ለመፍጠር የሞከሩ 57 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ለአሸባሪዎቹ የህወሓትና ሸኔ ቡድኖች በተለያዩ ህገወጥ መንገዶች ገንዘብ ሲያሰባስቡና ሲያስተላልፉ የነበሩ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በመፈጸም ህብረተሰቡን ለአመጽ ለማነሳሳት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ በአዲስ አበባ 51 እንዲሁም በአፋር ክልል 6 በድምሩ 57 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

ግብረሃይሉ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች ተሰማርተው ከአሸባሪዎቹ ህወህትና ሸኔ ቡድን ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በመፍጠር በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲያሰባስቡና ሲያስተላልፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ከተለያዩ ማስረጃዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አንድ አንድ ተጠርጣሪዎች በህግ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በመሰማራት ለሸብርተኛው የህወሓት ቡድን መረጃዎችን በመሰብሰብ በሚስጥር ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ እንዲሁም ለሽብር ቡድኑ የፋይናንስ ምንጭና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ለማድረግ በህቡእ ሲንቀሳቀሱ በተደረገው ክትትል መታወቁን ያመለከተው የጋራ ግብረ ሃይሉ መግለጫ፤ በቅርቡም ከአሜሪካና ከሌሎች የጁንታው ተባባሪዎች የተላከላቸውን መጠኑ በርከት ያለ ገንዘብ ለሽብር ቡድኑ አፈቀላጤ ለጌታቸው ረዳ እና ለሌሎችም የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በድብቅ ወደ መቀሌ ለመላክ ሙከራ እያደረጉ እያለ በተደረገባቸው ጥብቅና ሚስጥራዊ ክትትል መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህም ተጠርጣሪዎች መካከል ፍቃዱ ረዳ የተባለው ግለሰብ በአዲስ አበባና በመቀሌ ቅርንጫፍ ባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የተሰጠውን ሃላፊነት በሽፋንነት በመጠቀም ለአሻባሪው የህወሓት ቡድን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር መዋሉን መግለጫው አስታውቋል፡፡

መረሳ ገ/ስላሴ፣ ኑር አበባው ካሳዬ፣ አማን አህመድ፣ ሃብቶም ደሳለኝ፣አብዲሳ ጫላ የተባሉትና ሌሎችም ከሽብር ቡድኖቹ ጋር በፈጠሩት ሚስጥራዊ ትስስር ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥ አብዛኛዎቹ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን አባላት ሀብቶች ለማሸሽ፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሽፋንነት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለመላክ ጥረት ሲያደርጉ እንዲሁም መረጃዎች የማሰባሰብ ስራ ለማከናወን ሲሞክሩ እንደነበር መግለጫው አመልክቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን አመራሮች ጋር ያደርጉት የነበረውን ግንኙነት በተመለከተ ማስረጃዎች መያዛቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ ከሸኔ አባላት ጋርም በህቡዕ መልዕክት በመለዋወጥ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ያሴሩ እንደነበር አስታውቋል፡፡

መግለጫው አክሎም፤ ተጠርጣሪዎቹ ገንዘብና ወታደራዊ አልባሳትን ከአዲስ አበባ ከተማ በማሰባሰብ በአፋር ክልል ለቡድኑ ለማድረስ ሲሞክሩና ከዛም ተልዕኮ በመቀበል አዲስ አበባ መጥተው፤ ከሸኔ ቡድን አባላት ጋር ግንኙነት ፈጥረው የሽብር ተግባር ለመፈጸም በተለያዩ ግለሰቦች ቤት ምክክር ሲያደርጉ እንደነበር ጠቁሟል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከሽብር ቡድኖቹ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ ሚስጥራዊ ክትትል ሲደረግ እንደነበር የጠቆመው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፤አዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋሉት የህወሃት የሽብር ቡድን ደጋፊዎችና ተላላኪዎች አፋር ክልል ላይ ከተያዙት 6 ግለሰቦች ጋር በቀጥታ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ ከህወሃት የሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በተለያዩ ስልቶች እየተገናኙ የጥፋት ተልዕኮ ጭምር ለመፈፀም በድብቅ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም የጋራ ግብረኃይሉ ገልጿል።

በተያያዘ እነዚሁ ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችንና የግንባታ ዕቃዎችን በመጋዘን በማከማችት እጥረት እንዲፈጠርና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በማድረግ እንዲሁም ዜጎች ግብር እንዳይከፍሉም በህቡዕ ቅስቀሳ ላይ በመሰማራት ህብረተሰቡ ለአመጽ እንዲነሳሳ ጥረት ሲያደርጉም እንደነበር የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡

ሽብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በራሳቸውና በህቡዕ ካደራጇቸው አባሎቻቸው ጋር በመቀናጀት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመፈፀም የሚሞክሯቸው ጥቃቶች፣ትንኮሳዎችና ወረራዎች በውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎችም ጭምር የሚደገፉ መሆናቸውን የተገነዘበው መላው ዜጋ፤ ግለሰቦቹ የተለያዩ ሽፋኖችን በመጠቀም ለመንቀሳቀሰ ቢሞክሩም ሴራዎቹን በማክሸፉ ሂደት የደህንነትና የጸጥታ አካላት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ሲያደርጉ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እገዛ ማድረጉን በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

የአገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ በሽብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት እና በጀሌዎቻቸው የሚቃጣውን ጥቃትና ወረራ እንዲሁም በውጭ ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚቀነባበረውን ሴራ ለማክሸፍ በደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እየተወሰደ ያለው የተቀናጀና ተከታታይ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆመው መግለጫው፤ ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታና ለደህንነት አካላት የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡