6ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ተመረቀ

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ 1 መስታወት ፋብሪካ አካባቢ የተገነባ 6ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ  የከተማ አስተዳደሩ የምገባ ማዕከላትን ከማደራጀት ባለፈ በአስቸጋሪ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን አመርቂ ወጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎፈቃድ ስራ 850 የአቅመ ደካማ  ቤቶች ጥገና፣ 316 ወላጅ አልባ ህፃናት ወላጅ እንዲያገኙ ማድረግ  እና 11ሚሊየን በላይ ችግኞች እና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የምገባ ማዕከል በቀን ከ1ሺህ በላይ ዜጎችን የሚመግብ ሲሆን ለበርካታ ሴቶችና እናቶች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት በበጎፈቃድ ስራቸው የሚታወቁት  አቶ ሽኩር ኸይረዲን ለአንድ ዓመት የማዕከሉን የምገባ ወጪ እንደሚሸፍን በመርሐግብሩ ተናግረዋል፡፡