በኢትዮጵያ 3ኛው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ማሳያዎች ተገኙ

ነሃሴ 18/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ሦስተኛው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ማሳያዎች በመኖራቸው ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ሦስተኛው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ማሳያዎች አሉ።

ባለፈው ሳምንት ብቻ 5 ሺ 547 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ 510 በጽኑ መታመማቸውንና 66 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም የመያዝ ምጣኔ ከጥቂት ወራት በፊት ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ የነበረው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ወደ 12 በመቶ ያደገ መሆኑን አብራርተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ በቀን አንድ ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዙ የሚያመለክተው ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ነው።

ቅዳሜ ዕለት የተመዘገበው ቁጥር ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከታዩት ከፍተኛው መሆኑ ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ ችግሩ ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ሳይንሳዊ ትንበያዎች እንዳሉ ዶክተር ሊያ አመልክተዋል።

የቫይረሱን ሥርጭት በተመለከተ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በስብሰባዎች፣ በእምነት ተቋማትና በማህበራዊ መስተጋብሮች አካባቢ መዘናጋቶች መኖራቸው ይስተዋላል።

“የችግሩ መውጫ ቁልፍ በእጃችን ነው” ያሉት ዶክተር ሊያ፤ ስብሰባዎችን መቀነስ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የእጅ ንጽህናንና ክትባት በመከተብ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።

በአገሪቷ የቫይረሱን ስርጭትን ለመከላከል እየተሰጠ ያለው ክትባት የሚመለከተው ሁሉ መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል።

በብዛት እየተሰራጨ ያለው ቫይረስ በአብዛኛው የሚያጠቃው ያልተከተቡ ሰዎችን መሆኑንም ጠቁመዋል።

ክትባቱን በአዲስ አበባ በሁሉም ጤና ጣቢያዎችና ክልሎችም እየተሰጠ መሆኑን ዶክተር ሊያ አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በዓለም የጤና ድርጅት የጸደቁ ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች ክትባት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በዓለማቀፍ ደረጃ እስካሁን 4 ነጥብ 84 ቢሊዮን ሰዎች ክትባት የተሰጠ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በየቀኑ 34 ነጥብ 95 ሚሊዮን ሰዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታል።