አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የባህልና ቅርስ ባለስልጣን ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – በባህሬን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የባህልና ቅርስ ባለስልጣን ፕሬዚዳንት ሜይ ቢንት መሐመድ አልከሊፋ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በሚጠናከሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅት አምባሳደር ጀማል በክር ኢትዮጵያ ባለብዙ ባህል፣ አርትና ሙዚቃ አርኪዮሎጂ፣ ታሪክ ባለቤትና ቀደምት ስልጣኔ ያላት አገር በመሆኗ በዚህ ዘርፍ ይበልጥ ከባህሬን ጋር በቅንጅትና በትብብር የሚሰራበትን ነጥቦች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች ባለቤት በመሆኗ በቅርብና በሩቅ ካሉት አገራት ጋር የሚያስተሳስር የአብሮነትና የትብብር ተምሳሌት በመሆኗ፤ ይህ እሴትና ባህል እንዲጠናካር ለማድረግ የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም የባህሬን የባህልና የቅርስ ባለስልጣን ከአቻው የኢትዮጵያ የምርምርና የባህል ቅርስ ባለስልጣን ጋር በትብብር ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ አንስተው ተወያይተዋል፡፡

የባህሬን የባህልና የቅርስ ባለስልጣን ፕሬዚዳንት  ሜይ ቢንት መሐመድ አልከሊፋ በበኩላቸው ስለተደረገላቸው ገለፃ አመስግነው፣ ኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ፤ የቅርስና የባህል ባለቤት በመሆኗ በዚህ ዘርፍ ብዙ ተሞክሮ ልታበረክት የምትችል አገር መሆኗን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የባህል፤ አርትና የሙዚቃ ዝግጅቶች የተዘጉ ቢሆንም በቅርቡ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚጀምሩ በመሆኑ የኢትዮጵያ ባህል፤ አርትና ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ከቆንስላ ጽ/ቤቱ ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጐታቸውን ገልጸዋ፡፡

በተጨማሪም በባህሬን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ባህላቸውን ለማስተዋወቅ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ባለሥልጣኑ በሙሉ አቅም የሚደግፋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱም ኃላፊዎች የሁለቱ አገራት የባህላዊና፤ አርት፤ ሙዚቃ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚጠናከርበት ዙሪያ በትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት መፍጠሩን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።