አልማ 220 ኩንታል የስንዴ ዱቄት በንፋስ መውጫ ለተጎዱ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረገ

ነሐሴ 23/2013 (ዋልታ) – የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት 220 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ህወሓት በከፈተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የንፋስ መውጫ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረገ።

የአልማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አራጋው ታደሰ  ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት የህወሓት አሸባሪ ቡድን የንፋስ መውጫ ከተማን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ንጹሃን ዜጎችን በመግደል፣ ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ህብረተሰቡ ለእለት ምግብ እጦት እንዲጋለጥ አድርጓል።

ማህበሩ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የገዛውን 220 ኩንታል የስንዴ ዱቄት በከተማው ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በድጋፍ ማስረከቡን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ከወልድያ፣ ከቆቦ፣ ከአላማጣ፣ ዋግ ኽምራና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴና ኮምበልቻ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች 327 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ማቅረቡቸውን አስታውሰዋል።

ማህበሩ ከአባላት፣ ከረጅ ድርጅቶችና ከደጋፊዎቹ ሃብት በማሰባሰብ በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከእለት ምግብ አቅርቦት እስከ ማቋቋም ድጋፍ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አለምነው ክንዴ በበኩላቸው ቡድኑ በፈጸመው ግፍ ከ8 ሺህ 500 በላይ የቤተሰብ አባላት የሆኑ ከ25 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ለእለት ምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ጠቅሰዋል።

የአማራ ልማት ማህበር ለወገኖቹ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ለተጎዱ ነዋሪዎች በፍትሃዊነት እንደሚከፋፈል ጠቁመው ሌሎች ረጅ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ መምሪያ ሃላፊና የዞኑ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስማረ ጀንበር በዞኑ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ለማወቅ መረጃ እየተሰበሰበ ነው፡፡

“ችግሩን ከግምት ውስጥ ያስገባ ድጋፍ ከህብረተሰቡና ረጅ ድርጅቶች ይሰበሰባል” ብለዋል።

ቡድኑ ከእለት ምግብ ጀምሮ ነዋሪው በጎተራው ያጠራቀመውን የምግብ እህል፣ አልባሳት፣ ጥሬ ገንዘብና ሌሎች ሃብትና ንብረቶችን ከመዝረፍ ባሻገር መውሰድ ያልቻለውን እያወደመ መሄዱን ተናግረዋል።

ቡድኑ ከሌሎች አካባቢዎች ይልቅ በንፋስ መውጫ ረዥም ጊዜ መቆየቱን ጠቁመው ያደረሰው ጉዳትም በቆይታው ልክ ከፍተኛ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

ህብረተሰቡ ከእለት ምግብ ጀምሮ እስከ አልባሳት ድረስ ለችግር የተጋለጠ በመሆኑ ድጋፍ የሚያሰባስብ አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙን አመልክተዋል።

ሰሞኑን የደብረ ታቦር ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ 200 ኩንታል ዱቄት ለነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው አልማ ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።