ተመራቂዎች ሀገር የመታደግ ተሳትፏቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ተገለጸ

ነሐሴ 23/2013 (ዋልታ) – ጠላት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር ለማምከን መላ ኢትዮጵያዊያን በተነሱበት ወቅት እየተመረቁ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሀገራቸውን ለመታደግ ተሳትፏቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታከለ ታደሰ (ፕ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ትናንት ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በዋናው ግቢ ያስመረቀው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ደግሞ በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ በ4ኛ ዙር መርሃ ግብሩ 398 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

ተማሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ እና በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በንግግራቸው የተማሪዎች ምረቃ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገር ለማፍረስ የሚደረግን የጠላት ኃይሎች እንቅስቃሴ ለማምከን የሕዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በጎለበተበት እና የኅዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በተሳካበት ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህም “የሀገሪቱን መፃዒ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን እና ዘላቂ ውጤት ለማስመዝገብ ሁላችንም ተግተን መስራት አለብን” ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ እና የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ከብዙ ፈተናዎች መታደግ ግድ ይላል ብለዋል።

የዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ዲን ዶክትር ሽመልስ አርጋው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የፀጥታ ስጋት ሳይበግራቸው ትምህርታቸውን በስኬት ላጠናቀቁ ተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውንም ዩኒቨርሲቲው የላከልን መረጃ ያመለክታል።