አገር ዐቀፍ የፆም ፀሎት መርሃ ግብር ታወጀ

ነሐሴ 27/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምዕመናን 5ቱን የጳጉሜ ቀናት በፆም እና ፀሎት እንዲያሳልፉ አገር ዐቀፍ የፀሎት መርሃ ግብርን አወጀ፡፡

የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ እንዲሁም መጪውን 2014 አዲስ አመት በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሰኞ ጳጉሜ 1 በአገር ዐቀፍ ደረጃ በአገርም ይሁን ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላም ፈጣሪያቸውን እንዲለምኑ ጠይቀዋል።

2013 በኢትዮጵያ ፈታኝም በጎ ነገሮች የተከሰቱበት ነበር ያሉት የበላይ ጠባቂ አባቶች የአንበጣ መንጋ ክስተትን፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እንዲሁም የሰላም እጦትን፣ ስደት እና የአንድነት መሸርሸርን አልፈን የኅዳሴ ግድብን 2ኛ ሙሌት ማሳካታችን የኢትዮጵያዊያንን የማይበገር እና የማይሸረሸር አንድነት ያሳያል ብለዋል።

(በቁምነገር አህመድ)