ለአትሌት ሰለሞን ቱፋ ሽልማት

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) በቶኪዮ ኦሎምፒክ የቴኳንዶ ውድድር ተሳታፊ የነበረውና የዲፕሎማ ደረጃ ተሸላሚው አትሌት ሰለሞን ቱፋ የ150 ሺሕ ብር ሽልማት ተበረከተለት።

አትሌቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከሰሞኑ ባዘጋጀው የምስጋናና ሽልማት መርሃ ግብር ላይ ረስቶኛል ሲል ቅሬታውን በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሮ ነበር። ሽልማቱ ቀርቶ በተሳታፊነት እንኳን እንድገኝ አልተደረኩም ሲልም መውቀሱ ይታወሳል።

ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ልዑክ በተለያዩ ወገኖች ሽልማት ሲበረከት የሰነበተ ሲሆን፤ ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በነበረው ሽልማት ላይ አትሌት ሰለሞን መካተቱ ተገልጿል።

“ትናንት በተካሄደው የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ተሳታፊ የኢትዮጵያ ልዑክ አባላት የማበረታቻ እና የእውቅና ፕሮግራም በወርልድ ቴኳንዶ በ58 ኪሎ ግራም በመሳተፍ 7ኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው ሰለሞን ቱፋ በዲፕሎማ ደረጃ የ150 ሺሕ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።” ሲል የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን በፌስ ቡክ ገፁ አስነብቧል።