በአገራዊ ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር

ነሐሴ 29/2013 (ዋልታ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ምክክር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ገለፃ አድርገዋል።

በንግግራቸውም ምንም እንኳን በጦርነቱ አሸባሪው ሕወሓት ከፊት ቢሰለፍም በርካታ የውስጥና የውጭ ፀረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች ይገኙበታል፤ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኅብረት የሚያስፈልግ በመሆኑ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ውይይቱ አገርን ለማሻገር በሚደረገው ጥረት አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

እነዚህ  ኃይሎች ታሳቢ ያደረጉት ኢትዮጵያዊያን በብሔርና በፓለቲካ አስተሳሰብ የተከፋፈሉ በመሆናቸው አገሪቱን ከመፍረስ አይታደጉም የሚል ቅዠትን ቢሆንም ነገር ግን አገርን ለመታደግ ኢትዮጵያዊያን ልዩነትን ገሸሽ አድርገው እየተረባረቡ ይገኛል ብለዋል።

ይበልጥ የተናበበ እና የተደራጀ ሥራ በመስራት ጠላቶቻችን ለማሳፈር፣ አገርንም ለማሻገር ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች አበረታች ሥራዎች እየሰሩ በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግሥት ሚና ምን ይመስላል በሚል የመነሻ ጽሑፎችን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዛዲግ አብረሃ እና በኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) እየቀረበ ይገኛል።

(በደረሰ አማረ)