“የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያልተቋጨ የቤት ሥራ” መጽሐፍ ምረቃ

ነሐሴ 29/2013 (ዋልታ) “የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፤ ያልተቋጨ የቤት ሥራ” የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ።
በበለጠ በላቸው (ዶ/ር) ተጽፎ በኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ የታተመው መጽሐፍ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ የዘርፉ ባለሞያዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ነሐሴ 28 አመሻሽ በሂልተን ሆቴል ተመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የመክፈቻ መልእክት ያስተላለፉት ፅጌ ገብረማሪያም (ዶ/ር) አገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ ምድረ ቀደምት መሆኗን ጠቅሰው በየጊዜው ከውጪ ጠላቶች ሊወሯት ሲሞክሩ እና የውስጥ ግጭቶችን ተጠቅመው አንዳንድ የጎረቤት አገሮች ድንበሯን ቢደፍሩም በኢትዮጵያዊ አንድነት እና ወኔ ወረራዎች ተቀልብሰው ዳር ድንበሯ ተጠብቆ እንደቆየ ተናግረዋል።
አያይዘውም በዕለቱ የተመረቀው መጽሐፍ በዓለም ዐቀፍ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ለሚሰሩና ጥናት ለሚያካሂዱ አካላት ከፍ ያለ ቁምነገር የያዘ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የድንበር አከላለል በተመለከተ በተለያዩ ዘመናት የነበሩ ሂደቶችን፣ የተደረጉ ጥረቶችን፣ የተመዘገቡ ድሎችን እና የገጠሙ እክሎችን በሰፊው የተነተነ መረጃ በመጽሐፉ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ በበኩላቸው የአገሪቱን ዳር ድንበር በተመለከተ እስካለንበት ዘመን ድረስ በአግባቡ በመሬት ላይ የተከለለው ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ፣ ገና ብዙ የሚቀር የቤት ሥራ መኖሩን በማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል፡፡