የዳውሮ ዘመን መለወጫ ‘ቶኪ በዓ’ በዓል መከበር

የዳውሮ ዘመን መለወጫ ‘ቶኪ በዓ’ በዓል 

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) የዳውሮ ዘመን መለወጫ ‘ቶኪ በዓ’ በዓል በዞኑ የነገስታት መናገሻ በሆነው ኮይሻ ካቲ ጋጿ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የዘንድሮ የዘመን መለወጫ በዓል የሀገር ክብር ለማስጠበቅ እየተዋደቁ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በማሰብ እንዲሆንና በዞኑ ከእይታ ውጪ የሆኑ ከ450 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የ16 ነገስታት መናገሻን መልሶ ለማልማት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በሥፍራው የተገኙ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ ‘ቶኪ በዓ’ በዓል አከባበር በየዓመቱ እያደገና እየሰፋ የመጣ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን አንድ ላይ ተሰብስቦ ከማክበር ይልቅ የመከላከያ ሠራዊትን በማሰብ እና እየጠፉ የሚገኙ ቅርሶችን ለመታደግ ጉብኝት በማድረግ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ባህሉን ተንከባክቦ እና ከዘርፉም ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ዳዕሞ ደስታ ከገበታ ለአገር ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የብሄሩን ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅና ተንከባክቦ ለማቆየት የተጀመሩ ተግባራትን በጥናትና ምርምር ሥራዎች በማስደገፍ ለበለጠ ተጠቃሚነት ተገቢ የሆኑ ድጋፎችን በማድረግ መምሪያው እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ከፍታው በተለይም አሁን ላይ ከገበታ ለአገር ፕሮጀክት ጋር የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በትኩረት መሠራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ በነገስታቱ መናገሻ የሚገኙ የድንጋይ ላይ ገበጣ፣ የድንጋይ ሙቀጫ፣ የድንጋይ እንስራ፣ የድንጋይ ላይ እሳት ማንደጃ፣ የነገስታቱ ዙፋንና መናፈሻዎች መጎብኘታቸውን የደሬቴድ ዘግቧል።