የአየር መንገዱ ወደ ሱዳን ያጓጓዛቸው የአደን መሣሪያዎች ሕጋዊነት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ያጓጓዛቸው የአደን መሳሪያዎች አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ያላቸው ሕጋዊ መሣሪያዎች መሆናቸውን ገለጸ።

የአደን መሣሪያዎቹ መጓጓዝ ሕጋዊነትን የሚያረጋግጥ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጻፈ ደብዳቤ መኖሩንም አየር መንገዱ ጠቁሟል።

በመሆኑም የሱዳን የዜና ወኪል ‘ሱና’ የአደን መሣሪያዎች በሱዳን መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም ያለመ ነው የሚለው ዘገባ “ሐሰት” ነው ሲል አየር መንገዱ አስተባብሏል።

አየር መንገዱ መሣሪያዎቹ ለአደን አገልግሎት የሚውሉና አስፈላጊው የደኅንነት ማጣሪያ እስኪደረግላቸው ድረስ በአዲስ አበባ ለበርካታ ጊዜያት መቆየቱን አብራርቷል።

ይህንንም ተከትሎ የአደን መሣሪያው ተቀባይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያዎችን እንዲልክ ወይንም 250 ሺህ ዶላር እንዲከፈለው በሱዳን ፍርድ ቤት አየር መንገዱን መክሰሱን አመላክቷል።

አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ደኅንነት ኃላፊዎች የማጣራት ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የአደን መሣሪያውን ለማጓጓዝ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በሱዳን ለሚገኘው ተቀባይ ጦር መሳሪያውን ማጓጓዙን ከየኢትዮጵያ አየር መንገድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።