ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመተከል ሰላም አስከባሪ ልዩ ኃይሎችን መጎብኘት

ጳጉሜ 02/2013 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመተከል ዞን ሰላም ለማስከበር ተሰማርተው የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን ጎበኙ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የኢትዮጵያን ትንሳኤ የማይፈልጉ ኃይሎች ክብሯን ለመንካት ሊሞክሩ ይችላሉ እንጂ በመከላከያ ሰራዊት እና በክልል ልዩ ኃይሎች ጀብድ ጁንታው ተወግዶ ወደ ከፍታ ማማ እንወጣለን ብለዋል።

የሲዳማ ልዩ ኃይል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን ቀጣና ከሰራዊት ጋር በመሆን የጁንታ ተላላኪ ኃይሎችን በማሳደድ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመወጣት ላይ እንደሚገኙም  ተናግረዋል።

አክለውም በሰሜን ግንባር እና በመተከል ዞን በአሸባሪው ህወሃት የተከፈተውን ጦርነት በጋራ በመመከት መጪውን አዲስ ዓመት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በባህል፣ በልማትና በሰላም በጋራ እንደሚሰራም አውስተዋል።

የሲዳማ ክልል በመተከል ዞን ህግን ለማስከበር ለተሰማራው የሰራዊት አባላት 20 ሰንጋዎችን፣ አምቡላንስ እና ሌሎች ድጋፎችን አበርክቷል ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው፣ በቀጣናው የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መንግስት በውይይት ለመፍታት ጥረት ያደረገ ቢሆንም፤ የሽፍታው ቡድን ግድያን በመምረጡ አሁን ላይ ሰራዊቱ እየወሰደ ያለውን እርምጃ የክልሉ መንግስት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

በክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት በመሆኑ የሲዳማ ባለሃብቶች በፈለጓቸው አማራጭ ተሰማርተው ማልማት እንዲችሉ ፈቃደኛ መሆናቸውን አቶ አሻድሊ መናገራቸውን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።