ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች መመለስ

ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች

ጳጉሜ 04/2013 (ዋልታ) ከ153 ዓመት በፊት ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መመለሱ ተገለጸ፡፡

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጦርነት ላይ ይጠቀሙበት የነበረ የጦር ጋሻ፣ ከቆዳ የተሰራና በእጅ የተጻፈ የብራና መፅሀፍ ቅዱስ እሰከነመያዣው፣ ትልቅ እና አነስተኛ መስቀሎች፣ ጽዋ የሚወሰድበት ዋንጫ ከነማንኪያዎቹ፣ የጳጳስ አክሊል ከቀንድ የተሰሩና በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎችን ከነመስቀሉ በትላንትናው እለት መረከቡን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡

ቬሄራዜድ በመባል የሚታወቀው የዩናትድ ኪንግደም የበጎ አድራጎት ድርጅት ከለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርሶቹ ዙሪያ ወራትን የወሰዱ ድርድሮችን እና ለሽያጭ ቀርበው የነበሩትን ከገበያ እንዲነሱ በማድረግ ቅርሶቹ ለባለቤታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመለሱ ውሳኔ ላይ መደረሱን በርክክቡ ወቅት ላይ ተገልጿል።

ለንደን በሚገኘው አቴናም በተባለና የዩናይትድ ኪንግደም ልሂቃን ክለብ በተካሄደ የርክክብ ስነሥርዓት ላይ በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት ቬሄራዜድ በጎ አድራጎት ድርጅት ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ላደረገው ሰፊ ጥረት ምስጋና በማቅረብ፣ እነዚህ የሀገር ሀብቶች ከቅርስነት በላይ የኢትዮጵያን የጀግንነትና የሃይማኖት ታሪኮች ለትውልድ ጽኑ የሆኑ ማስታወሻዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን መልሰን እንድናገኝ የሚረዱን መለያዎቻችን ናቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ አኩሪ የሆነ ጥንታዊ እና ገናና ታሪክ ያለው አንድነቱን ጠብቆ ለመኖር የቅርሶቹ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቅርሶቹ ለሃገራችን መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ሲሆን ሌሎች በዘረፋ የተወሰዱ ቅርሶቻችን በዚህ መልክ በድርድር ለማስመለስ አስተዋፅኦ እንዳለው ያመለከተቱት አምባሳደር ተፈሪ በቀጣይነት በእንግሊዝ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ ከፍተኛ ድርድሮች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያና በእንግሊዝ ታሪካዊ የጋራ ግንኙነት ላይ መቅደላ የፈጠረውን መጥፎ አጋጣሚ በአዎንታዊነት ለማደስ እነዚህ በህገወጥ መንገድ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የቬሄራዜድ በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጣሂር ሻህ በበኩላቸው፣ ከቅርሶቹ መካከል የተወሰኑት በኤምባሲውና በሚመሩት በጎ አድራጎት ድርጅታቸው አማካይነት ለሽያጭ ከቀረቡበት የታገዱ መሆናቸውን ገልፀው፣ እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑ ለባለቤቱ እንዲመለሱ መደረጋቸው የሁለቱን ሀገሮች የቆየ ግንኙነት ወደተሻለ ጥልቅ ትስስር የሚያሻግር ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት በርክክብ ስነሥርአቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት “ይህ ቀን ለኢትዮጵያ የአንድነት ታሪክ አዲስ ምእራፍ የሚከፍት ነው ፤ጥንታዊ ታሪክ ያላትን ሀገር ቅርሶቿን በአግባቡ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉ የሃገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው” ብለዋል፡፡

ገጣሚና የማንቼስተር ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ለምን ሲሳይ በበኩሉ፣ “በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ያኮራኝ እለት ቢኖር ዛሬ ነው ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን እንኳን ደስ አለን” በማለት ታሪክ የሀገር መሰረት በመሆኑ የዛሬው ስነስርአት ለኢትዮጵያ ሌላ ምእራፍ ነው በማለት ተናግሯል፡፡

የተመለሱት ቅርሶች በትላንትናው እለት ወደ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የገቡ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት እንደሚላኩ ተገልጿል፡፡

ከሁለት አመት በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ጸጉር ከለንደን ወደ አገሩ መመለሱን  ከኢምባሲው የተገኘው መረጃ አስታውሷል።